Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለለቅሶ የተጣለ ድንኳን ጥሶ የገባ አውቶቡስ ባደረሰው ጉዳት የ3 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከጳውሎስ ሆስፒታል ወደ ሸጎሌ በሚወስደው መንገድ አለም ፀሐይ ድልድይ አካባቢ አንድ የከተማ አውቶብስ ለለቅሶ የተጣለ ድንኳን ጥሶ በመግባት ባደረሰው ጉዳት የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ።

አደጋው የደረሰው ትናንት ቅዳሜ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ሲሆን÷ በአደጋውን እስከ ትናንት ምሽት ድረስ የ3 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ20 በላይ ሰዎች ላይም ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡

በአደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው ተጎጂዎች መካከል የተወሰኑትን የአዲስ አበባ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቅድመ ሆስፒታልና አምቡላንስ አገልግሎት ባለሞያዎች ሕክምና እያደረጉላቸው ወደ-ሆስፒታል እንዳደረሷቸው ተጠቅሷል፡፡

የአዲስ አበባ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ እንደገለጹት÷ በድንኳን ውስጥ ለባለቤቷ ለቅሶ የተቀመጠችው በዚሁ አደጋ ወላጅ እናቷንም አጥታለች፡፡

ህይወታቸውን ያጡትና ጉዳት የደረሰባቸውም ሀዘንተኛዋን ለማጽናናት በድንኳን ውስጥ የተቀመጡ ናቸው ብለዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል በአስጊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙም እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን÷ ተጎጂዎቹ በአቤትና በራስ ደስታ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡

በትዕግስት ስለሺ

 

Exit mobile version