አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምን ጊዜም ቢሆን ለሠላምና ለንግግር የሚረፍድ ጊዜ የለም ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው፡፡
በሥነ- ሥርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር÷ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሄድ የነበረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሠላም ስምምነት እንዲቋጭ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለው የአኅጉራችን መርኅ በተግባር ተፈትሾ ውጤታማ እንደሆነ አሳይተናል ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ ስምምነቶቹ ወደ ተግባር ተቀይረው የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል በንግግራቸው፡፡
በሰሜኑ ሀገራችን ክፍል የነበረው ሁኔታ ለሀገራችን ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት ሆኖ አልፏል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የሰሜኑን ጦርነት በንግግር መፍታት መቻሉ ብዙ ዜጎችን ከዕልቂትና ሰቆቃ የገላገለና እፎይታን የፈጠረ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ከዚህ በኋላ በሀገራችን በጠመንጃ እና ኃይል ልዩነቶችን የመፍታት አማራጭ ማክተም እንደሚኖርበትና እንደሚችልም በተግባር ያሳየ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ከማንኛውም ኃይል ጋር ችግሮችን በመወያየትና በንግግር የመፍታት ቁርጠኝነት እንዳለው በተግባር ያስመሰከረበት ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፡፡
ምን ጊዜም ቢሆን ለሠላምና ለንግግር የሚረፍድ ጊዜ የለም ብለዋል ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ በንግግራቸው፡፡
በዮሃንስ ደርበው