አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታይዋን ከቻይና ጋር ሰላማዊ አብሮነት ትፈልጋለች ሲሉ ፕሬዝዳንት ፃይ ኢንግ-ዌን በግዛቲቱ ብሔራዊ ቀን ላይ ተናግረዋል፡፡
ታይዋን ከቻይና ጋር በነፃነት እና ባልተገደበ መስተጋብር ሰላማዊ አብሮነት ትፈልጋለች፤ ነገር ግን ደሴቲቱ ለሚመጡት ትውልዶች ዲሞክራሲያዊ ትሆናለች ሲሉ ፕሬዝዳንት ፃይ ኢንግ-ዌን ዛሬ ባደረጉት ንግግራቸው ገልፀዋል፡፡
ቻይና ግዛቴ ናት የምትላት ታይዋን ካለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ በደሴቲቱ አቅራቢያ ሁለት ዋና ዋና የጦር ልምምዶችን ጨምሮ የቤጂንግ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ጫና እየበዛባት መምጣቱ ይታወሳል፡፡
ይሁንና ውጥረቱ አይሎ ወደ ግጭት ከተቀየረ ዓለም አቀፋዊ ተፅእኖ ይኖረዋል የሚል ስጋት ማሳደሩ ተመላክቷል።
ለሁለት የስልጣን ዘመን ግዛቲቱን ያስተዳደሩት እና በጥር ወር በሚካሄደው ምርጫ እንደገና በፕሬዚዳንትነት መወዳደር የማይችሉት ፃይ፤ ከቻይና ጋር ተደጋጋሚ የድርድር ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም ቻይና ጥያቄያቸውን ውድቅ ማድረጓ ይነገራል፡፡
ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው ለታይዋን እየተደረገ ያለው ጠንካራ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ታይቶ ወደ ማይታወቅ ከፍታ ደርሷል ብለዋል፡፡
በታይዋን እና በቻይና መካከል ያለው ልዩነት በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት ያሉ ሲሆን፤ አሁን ያለውን ሁኔታ ማስቀጠል ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ማለታቸውን ዎርልድ ሞኒተር ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!