አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በስልክ በሚላክ መልዕክት ፓስፖርት የደረሰላቸው ተገልጋዮች ያለእንግልት እየተስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ቀደም ሲል ከነበረው አንጻር የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ተገልጋዮች ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በኦንላይን ያመለከቱ ሰዎች ፓስፖርታቸው እንደደረሰና መውሰድ እንደሚችሉ በስልካቸው በሚደርሳቸው መልዕክት መሠረት ሳይንገላቱ እየተስተናገዱ መሆናቸውን ነው ያነሱት፡፡
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በበኩሉ የተገልጋዮችን እንግልት ለመቀነስ የሚረዱ አሠራሮችን እየተገበርኩ ነው ብሏል፡፡
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ማስተዋል ገዳ ፓስፖርት የሚታተመው በውጭ ሀገር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በወቅቱ ከማቅረብ አንጻር ክፍተት መስተዋሉን ጠቁመዋል።
ታትመው የመጡ ፓስፖርቶችን ግን እንደተመዘገቡበት ቅደም ተከተል ተገልጋዮች እየወሰዱ ነው ብለዋል፡፡
ተገልጋዮች ቀደም ሲል በተያዘ ቀጠሮ መሰረት ወደ አገልግሎቱ ቢያቀኑ ተገቢውን አገልግሎት ላያገኙ ስለሚችሉ፥ በአዲሱ አሠራር መሠረት አጭር የጽሑፍ መልዕክት ሳይደርሳቸው እንዳይመጡ የማሳወቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።
በሌላ በኩል አስቸኳይ ፓስፖርት የሚፈልጉ ተገልጋዮች÷ አስቸኳይ ፓስፖርት የፈለጉበትን ምክንያትና ማስረጃ አሟልተው ሲቀርቡ ከሁለት እስከ አምስት ቀናት ፓስፖርት ማግኘት እንደሚችሉ ነው ያስታወቁት፡፡
በሲሳይ ጌትነት
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!