Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ በሚገኘው የግሪን አፍሪካ ኢነርጂ ጉባኤ እየተሳተፈች ነው

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን እየተካሄደ በሚገኘዉ የአፍሪካ አረንጓዴ የሃይል ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ኢትዮጵያን በመወከል በፈረንጆቹ ከጥቅምት 9 እስከ 13 ቀን 2023 እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ ላይ እይተሳተፉ ይገኛሉ።

ሚኒስትሩ በተሳተፉባቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት የሚኒስትሮች ከፍተኛ የውይይት መድረኮች ላይ÷ የአፍሪካ የኢነርጂ አቅርቦት ዋነኛ ተግዳሮትን፣ አማራጭ የፖሊሲ መፍትሔዎችን፣ ቀጠናዊ ትብብሮችን፣ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍን በተመለከተ ከተሳታፊዎች የቀረቡ ጥያቄዎችን መሰረት አድርገው አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም ከአየር ንብረት ለውጥ ስጋት አንጻር ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረትና አጠቃላይ አገራዊ የወደፊት እንቅስቃሴ በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ለአጎራባች ሀገራት የምታቀርበው ታዳሽ የሃይል አማራጭ ተሞክሮ ቀጠናዊ የኃይል ትሥሥርን አስመልከቶ በትብብር መስራት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ሶማሊያ የኃይል ሽያጭ እያደረገችና በቅርቡ ከደቡብ ሱዳን ጋር የተፈረመው የትብብር ማዕቀፍም ወደ ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት አምስት አመታት ከ32 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ተግባር በዋናነት የከርሰ ምድር ውኃ አቅምን በመጠበቅና በማሳደግ ረገድ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ለጉባኤው መናገራቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በጉባኤው ጥቅምት ወር ማገባደጃ ላይ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ላይም ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

Exit mobile version