አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የሚሳተፉበት 2ኛ ዙር የስልጠና መድረክ በዛሬው ዕለት በ10 የስልጠና ማዕከላት ተጀምሯል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ አመራሮቹን በክህሎት፣ በልምድ እና በእውቀት ለማብቃት ሰፊ ስራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ከምስረታው ጀምሮም በርካታ የስልጠና መድረኮችን በማዘጋጀት የፖለቲካ አመራሩ እንደፓርቲ የሚቀርጻቸው ስትራቴጂዎች፣ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ የማድረግ አቅሙ እንዲዳብር ለማስቻል ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም ነው የተነገረው፡፡
በዚህም የአመራሩን የዓላማና የተግባር አንድነት ማሳደግ የሚችሉ፣ ተልእኮን የመፈፀም አቅምን የሚያካብቱ፣ የህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት እሳቤን የሚያበለፅጉ ውጤቶች ሲመዘገቡ ተስተውለዋልም ነው ያለው ፓርቲው፡፡
በዛሬው የተጀመሩ የስልጠና መርሐ-ግብሮች ከዚህ በፊት የተገኙ ውጤቶችን ለማሳደግና አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለሙ እንደሆኑም አስታውቋል፡፡
የስልጠና ማዕከላቱ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በሐዋሳ፣ በአርባምንጭ፣ በጅግጅጋ፣ በባህርዳር፣ በሚዛን አማን፣ በደሴ፣ በጅማ እንዲሁም በሆሳዕና ይገኛሉ፡፡
ከስልጠናው ጎን ለጎን ውይይቶች እና የልምድ ልውውጥ የተሞክሮ መርሐ ግብሮች መዘጋጀታቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአዳማ ከተማ በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ስልጠና ላይ ከ2ሺህ በላይ አመራሮች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፥ በዚህኛው ዙር ከ12 ሺህ በላይ አመራሮች የስልጠናው ተሳታፊ ናቸው፡፡