Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ስለ ማህፀን በር ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች ምን ያህል ያውቃሉ?

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማህፀን በር ካንሰር ማለት በማህፀን ጫፍ ላይ ያልተለመደ የህዋስ እድገት ሲከሰትና ይህም በመላው የማህፀን ጫፍ አካባቢ ሲዛመት የሚፈጠር ህመም ነው፡፡

የማህፀን በር ካንሰር የሚያስከትላቸው ጉዳቶች የደም መርጋት፣ የደም መፍሰስ፣ ፊስቱላ፣ የሆድ ድርቀት፣ የመሽናት ችግር፣ መካንነት እና የውስጣዊ አካል ከጥቅም ውጪ መሆንና እነዚህን የመሳሰሉትን ጉዳቶች ያስከትላል።

ከዚህም አልፎ የማህፀን በር ካንሰር እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል ህመም ነው፡፡

ለመሆኑ ለማህፀን በር ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች ምንድናቸው (ለህመሙ ተጋላጭ የሚሆኑት እነማን ናቸው)?

ማንኛውም የግብረ ስጋ ግንኙነት ፈጽማ የምታውቅ ሴት ሁሉ ለማህፀን በር ካንሰር የመጋለጥ አጋጣሚ ሊኖራት ይችላል፡፡

ይሁን እንጂ በለጋነት ዕድሜ (ከ20 ዓመት እድሜ በታች) የግብረ ስጋ ግንኙነት የጀመሩ ሴቶች፣ ከተለያዩ ወንዶች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሴቶች፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም መዳከም ያጋጠማቸው ሴቶች (ለምሳሌ ኤች አይ ቪ በደማቸው ውስጥ ያለ)፣ እንዲሁም በአባላዘር በሽታ የተያዙ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡

የማህፀን በር ካንሰር ዋና ዋና ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የማህፀን በር ካንሰር ምንም አይነት የህመም ስሜትና ምልክት ሳያሳይ ከ15 እስከ 20 ዓመት ሊቆይ እንደሚችል ከአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሽታው ከተባባሰ በኋላ ግን ከወር አበባ ወቅት ውጭ የማህጸን ደም መፍሰስ፣ የወር አበባ ጊዜ የተራዘመና ከባድ መሆን፣ የመውለጃ ጊዜ ወይም ዕድሜ ካለፈ በኋላም የደም መፍሰስ ማጋጠም፣ ያልተለመደ ወይም ለየት ያለ ጠረን ያለው የብልት ፈሳሽ፣ ድካም፣ የወገብ ህመም፣ መክሳት፣ የሆድ ህመም እና የመሳሰሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡

የማህፀን በር ካንሰርን እንዴት መከላከል ይቻላል?

በየአምስት ዓመቱ አንድ ጊዜ የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ፣ በተጨማሪም ከ20 ዓመት ዕድሜ በታች የሚገኙ ሴቶች የማህጸን በራቸው ያልዳበረ በመሆኑ በለጋነት ዕድሜ የግብረ ስጋ ግንኙነት ያለመፈጸም፣ ኤች ፒ ቪ ክትባትን መከተብ፣ በአንድ መወሰን፣ የአባላዘር በሽታን መከላከል ዋነኞቹ የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ዘዴዎች ናቸው፡፡

Exit mobile version