አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጎልበት የሥራ እድል ፈጠራ እና የቴክኖሎጂ እንዲሁም የእውቀት ሽግግርን ማረጋገጥ የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና አዲል ቴክኖሎጂስና ሶሉሽን ማዕከል የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጎልበት ለስራ እድልና ሃብት ፈጠራ የሚያስችል ፕሮጀክት ልማት እንዲሁም የቴክኖሎጂ የእውቀት ሽግግርን ለማረጋገጥ በቀጣይ ስለሚደረጉ ድጋፎች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አማካሪዎች ስሜነህ ቀስቅስ (ዶ/ር) እና ሰለሞን በላይ (ዶ/ር)÷በዘርፉ ችግር ፈቺ፣ ሀብት ፈጣሪና አቅም አጎልባች ሀሳቦችን ይዘው ለሚመጡ አካለት ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
የአዳል ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ማዕከል የአከባቢን ብክለት የሚቀንስና ለግንባታ ዘርፍ የሚያግዝ፣ የውጭ ምንዛሬ ጫና የሚያቃልልና የስራ እድል በመፍጠር ገቢ እንዲያስገኝ በማሰብ የተጀመረ ነው ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና የስራ አመራር ኃላፊዎች በሸገር ዙሪያ ከተማ በገላን ክፍለ ከተማ የሚገኘውን የበላይነህ ክንዴ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮምፕሌክስ ጎበኝተዋል።
ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷በኤሌትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም ላይ የተሰማራው የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ማዕከሉ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ ማገዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የመኪና ማምረቻ እና መገጣጠሚያ ድርጅቱ ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው÷ከድህነት ለመውጣትና ሃብት መፍጠር እንዲቻል በትብብር መስራት ያስፈልጋል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በቀጣይም ሚኒስቴሩ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በኤሌትሮኒክስ ግብይት፣ኢንዱስትሪውን በማስተዋወቅ እንዲሁም በጥናትና ምርምር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡