Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሐረርን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐረር ከተማን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በሰጡት መግለጫ ÷ ሐረር ከተማን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንዲሁም ለቱሪስቶች አመቺ እንድትሆን የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ከተማዋ ሙዚዬሞችን ያቀፈች በመሆኑ የቱሪዝም ሎጎ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን ነው ያስረዱት፡፡

የጅብ ትርዒት ማሳያ ስፍራን ለቱሪስቶች ምቹ ማድረግ የሚያስችል ኢኮ ፓርክ ግንባታ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማሰራት ወደ ስራ መገባቱን ጠቅሰው÷ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከትርዒት ባሻገር የቱሪዝም ፍሰቱን ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ጉዳት የደረሰባቸው 6 ባህላዊ ቤቶች እና 2 ጥንታዊ አድባራት ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩየማደስ ስራ እንደሚሰራም አመላክተዋል፡፡

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስንና ሌሎች ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የህዝብን አብሮነትና አንድነትን የሚያጎለብቱ እንዲሁም ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ስራዎች ይሰራሉ ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የሐረሪ ቋንቋን ለማጎልበትም እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው÷በዘርፉ የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ይደረጋልም ብለዋል፡፡

Exit mobile version