Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሀሰተኛ ቼክ 75 ሚሊየን ብር በማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተከሰሱ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 5 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀሰተኛ ቼክ ከኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አ.ማ ለክፍያ የታዘዘ በማስመሰል 75 ሚሊየን ብር በማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተከሰሱ።

ተከሳሾቹ 1ኛ የጂግጂጋ ነዋሪ የሆነውና የኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤት ነው የተባለው ሀሰን መሐመድ፣2 ኛ ከአንደኛ ተከሳሽ ጋር ይሰራል የተባለውና በሸገር ሲቲ ከተማ ነዋሪ የሆነው አማረ ሚዴቅሳ እና በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አክሲዮን ማህበር ኩባንያ የቀድሞ የንብረት ክፍል ኃላፊ አዲሱ ጌትነት ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1 ሀ ና ለን እንዲሁም የሙስና አዋጅ 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 2 ለ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከባድ የማጭበርበር ሙስና ወንጀል ሁለት ክሶችን አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ሰዓት ገደማ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ሀሰተኛ የ75 ሚሊየን ብር ቼክ በማዘጋጀት ከፊትና ከኋላ በመፈረም ለኦሮሚያ ባንክ ፉሪ ቅርንጫፍ መሄዳቸው በክሱ ተዘርዝሯል።

በዚሁ በፉሪ የባንክ ቅርንጫፍ ከሄዱ በኋላም የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አክሲዮን ማህበር ኩባንያ ሂሳብ 75 ሚሊየን ብር ገንዘብ እንዲከፈላቸው የታዘዘ በማስመሰል በአንደኛ ተከሳሽ ስም በዚሁ ቅርንጫፍ በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ውስጥ 75 ሚሊየን ብሩ እንዲዘዋወርላቸው ሀሰተኛ ቼኩን ማቅረባቸው በክሱ ተመላክቷል።

በዚህ ጊዜ የባንኩ ሰራተኞች በጉዳዩ ላይ በመጠራጠር የቼኩ የክፍያ ትዕዛዝ ከኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ እንደታዘዘና እንዳልታዘዘ ለማረጋገጥ ለ3ኛ ተከሳሽ ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ 3ኛ ተከሳሽ ቼኩ ለክፍያ ከኩባንያው ለግለሰቦቹ እንደታዘዘ በመግለጽ 75 ሚሊየን ብር እንዲከፈላቸው ማዘዙን ገልጾ ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ አስፍሯል።

በዚህ መልኩ 75 ሚሊየን ብር ተከሳሾቹ ወደ ከፈቱት ሂሳብ እንዲዛወር በማድረግ በአጠቃላይ በዋና ወንጀል አድራጊነት ሀሰተኛ ሰነዶችን አዘጋጅቶ በመጠቀምና በማጭበርበር ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

ክሱ የቀረበለት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ክሱን ለመመልከት ለነገ ቀጠሮ ይዟል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version