አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን ከ14 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ ተገለጸ፡፡
ድጋፉን ያደረገው በአራት አጋር ድርጅቶች ጥምረት የተቋቋመው “ስዋን የሰብዓዊ ጥምረት” የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው ተብሏል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ ወቅት የዎርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የዋሽ ናሽናል ስፔሻሊስት አቶ ሸዋንግዛው አሰፋ÷ ድጋፉ የተደረገው ጉዳት ላጋጠማቸው 2 ሺህ 378 እማወራዎችና አባወራዎች ነው ብለዋል።
ድጋፉን ያደረጉት ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ ጥምረት÷ሴቭ ዘ ችልድረን፣ ዎርልድ ቪዥን፣ “አክሽን አጌንስት ሀንገር” እና የኖርዌይ የፍልሰተኞች ምክር ቤት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከድጋፉ ውስጥ ብርድ ልብስ፣ ሸራ፣የቤት እቃዎች እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስና ሌሎችም እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጋትሉዋክ ጋች ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት÷ ድርጅቶቹ በከተማው በደረሰ የጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።
ከተማ አስተዳደሩም ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡