አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጡት ካንሰር በዓለማችን ካሉ የካንሰር ዓይነቶች መካከል በገዳይነቱ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች መካከል የጡት ካንሰር 33 በመቶ ሲሆን፥ በበሽታው መያዝና መሞት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
የበሽታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ግንዛቤን በማሳደግ በሽታውን የመከላከል ጥረት ለማሳደግ ጥቅምት ወር ስለጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር እንዲሆን የዓለም ጤና ድርጅት ወስኗል፡፡
ይህን አስመልክቶም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከካንሰር ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሙሉጌታ ካሳሁን ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ዶክተር ሙሉጌታ በዚህ ወቅት እንዳሉትም፥ የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘ የካንሰር ዓይነት ነው፡፡
በጡት ካንሰር የሚያዙትም 99 በመቶ ሴቶች ሲሆኑ፥ አልፎ አልፎም በወንዶች ላይ እንደሚከሰት ይነገራል፡፡
የጡት ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች፡-
• በዘር (ከ5 እስከ 10 በመቶ ሊከሰት የሚችል)፣
• ዘግይቶ መውለድ፣
• አለመውለድ፣
• እድሜ መጨመር፣
• ጡት አለማጥባት፣
• የወር አበባ በቶሎ አለማየት ወይም መዘግየት፣
• አላስፈላጊ ውፍረትና የመሳሰሉ እንደሆኑ የህክምና ባለሙያው አንስተዋል፡፡
ምልክቶች
• በቆዳ ላይ የሚታይ የቀለም ለውጥ፣
• የጡት ጫፍ መሰርጎድ፣
• የጡት ጫፍ ቁስለት፣
• ሳል (የመሰራጨት ምልክት)፣
• የጀርባ ህመም (የመሰራጨት ምልክት)፣
• በላይኛው የቀኝ ጎን ሆድ ህመም መኖር (የመሰራጨት ምልክት)፣
• ጡት አካባቢ (በብብት ወይም በአንገት ስር) የሚፈጠር እብጠት፣
• ከጡት ጫፍ የሚወጣ የተለየ ፈሳሽ እና የመሳሰሉት ተጠቃሽ እንደሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም አንዲት ሴት ጡቷን ቢያንስ በወር አንዴ በመመልከት ምልክቶቹ አሉ ወይም የሉም የሚለውን ማየት አለባት፡፡
ከነዚህ ምልክቶች መካከል ከታዩባት በአፋጣኝ ወደ ህክምና መሄድ እንዳለባትም ዶክተር ሙሉጌታ ካሳሁን አሳስበዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በተለይም ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች በዓመት አንዴ የጡት ካንሰር ምርመራ ማድረግ እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት፡፡
አክለው እንዳሉትም፥ የጡት ካንሰር ከተከሰተም እንደየደረጃው ህክምና እንደሚሰጥ ጠቅሰው፥ የሃኪም ቅድመ ምርመራ፣ የማሞግራፊ አልትራሳውንድ ምርመራ፣ ናሙና ምርመራ፣ የቀዶ ህክምና፣ ኬሞቴራፒ፣ የጨረር ህክምና፣ የሆርሞን ህክምና እና የመሳሰሉት ህክምናዎች ይደረጋሉ፡፡
#Ethiopia #breastcancerawareness #WHO #health
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!