Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አቶ አብነት ገ/ መስቀል በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቻ 15 ቀን ተሰጠ

 

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለሃብቱ አቶ አብነት ገ/ መስቀል በተጠረጠሩበት የ1 ሺህ 971 ካሬ ሜትር የይዞታ መሸጥ ለግል ጥቅም ማዋል ሙስና ወንጀል ክስ መመስረቻ 15 ቀን ተሰጠ።

ክስ መመስረቻውን የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በነበረው ቀጠሮ አቶ አብነት በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ለማድረግ ባቀረበው ጥያቄ መነሻ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ ክርክርን መርምሮ የተጨማሪ የማጣሪያ ጊዜ እንደሚያስፈልግ በማመን የ10 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዶ ነበር።

በዛሬው ቀጠሮ ደግሞ ፖሊስ የምርመራ ስራውን ማጠናቀቁን ጠቅሶ የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ ማስረከቡን ጠቁሟል።

የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ከፖሊስ የተረከበውን የምርመራ መዝገብ ተረክቦ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ጠይቋል።

በአቶ አብነት ጠበቆች በኩል ደግሞ ተጨማሪ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ህግ ሊሰጥ አይገባም የሚሉ የመከራከሪያ ነጥቦችን አንስተው ተከራክረዋል።

ዐቃቤ ህግ ጉዳዩን አስቀድሞ የሚያውቀውና ከዚህ በፊት የእግድ ዳኝነት የጠየቀበት ጉዳይ ላይ እንደአዲስ ክስ መመስረቻ መጠየቁ አግባብ አይደለም በማለት ተቃውመው ተከራክረዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጠርጣሪው ከተጠረጠሩበት ወንጀል አንጻር ክስ መመስረቻ ጊዜ መስጠት አስፈላጊነትን በማመን የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ፈቅዷል።

ጠበቆቻቸው የተሰጠው ብይን ተገቢነት እንደሌለው ለችሎቱ አሳውቀው ይግባኝ እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version