Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በ11 ከተሞች በ102 ሚሊየን ዶላር የ’’ዲስትሪቢዩሽን’’ መስመር መልሶ ግንባታ ስራ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ11 ከተሞች በ102 ሚሊየን ዶላር የዲስትሪቢዩሽን መስመር መልሶ ግንባታ ስራ ሊጀመር እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በዲስትሪቢዩሽን መስመሮች እርጅና ምክንያት በከተሞች አካባቢ የኃይል መቆራረጥ እያጋጠመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ በተመረጡ 11 ከተሞች የዲስትሪቢዩሽን መስመር መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ስራ እየተሰራ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በ57 ሚሊየን ዶላር 4ኛው ምዕራፍ የዲስትሪቢዩሽን ኔትዎርክ ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል ፡፡

የፕሮጀክት ወሰኑ 19 ኪሎ ሜትር አዲስ የመሬት ውስጥ ተቀባሪ መካከለኛ መስመር ፣ 9ኪሎ ሜትር አዲስ አየር ላይ ተንጠልጣይ መካከለኛ መስመር እንዲሁም 647 ኪሎ ሜትር የነባር የአየር ላይ ተንጠልጣይ መስመሮች ዕድሳት እንደሚከናወንም ገልጸዋል ፡፡

እንዲሁም የ2 ሺህ አዲስ ትራንስፎርመሮች ተከላ እና የሦስት አዲስ ስዊችንግ ስቴሽኖች ተከላ ስራ እንደሚካሄድ ጠቅሰው፥ ተጨማሪ የ2 ሺህ ነባር ትራንስፎርመሮች እድሳት ስራ እንደሚከናወንም አስረድተዋል።

በአሶሳ ፣ አምቦ ፣ ጅግጅጋ ፣ ነቀምት ፣ ደብረብርሃን ፣ ቢሾፍቱ ፣ አሰላ ፣ ዲላ ፣ ሆሳዕና እና ሱሉልታ ከተሞች በ45 ሚሊየን ዶላር ተመሳሳይ የኔትወርክ ማሻሻያ ስራ እንደሚካሄድም ነው የተናገሩት።

ፕሮጀክቱ በሦስት ሎት ተከፍሎ የሚከናወን ሲሆን ፥ በአጠቃላይ የ200 አዳዲስ ትራንስፎርመሮች እና የ1 ሺህ ትራንስፎርመሮች መልሶ ግንባታ ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል ፡፡

ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የሚከናወነው ይህ የፕሮጀክት ስራ ሲጠናቀቅ በከተሞቹ የሚኖረውን የሃይል መቆራረጥ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀርፈውም አቶ መላኩ አንስተዋል ፡፡

በሌላ በኩል በደብረማርቆስ፣ ሻሸመኔ የወላይታ ሶዶ የሐረር እና የኮምቦልቻ ከተሞች የኔትወርክ ማሻሻያ መልሶ ግንባታ ሂደት 79 በመቶ ደርሷል፡፡

በተጨማሪም 2ኛው ዙር የስማርት ሜትር የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ቅየራ ሥራ ሊጀመር ሲሆን ፥ ለዚህ የሚውል 45 ሺህ ስማርት ቆጣሪ ሀገር ውስጥ መግባቱንም አውስተዋል።

አሁን ላይም ሥራውን ለመጀመር የሚያስችል መረጃዎችን የማጥራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በመጀመሪያ ዙር ከ4 ሺህ በላይ ነባር ቆጣሪዎች በስማርት ቆጣሪዎች የተቀየሩ ሲሆን ፥ ይህም የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻልና የኃይል ብክነትን ለመቀነስ ረድቷል ነው የተባለው፡፡

በመሳፍንት እያዩ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version