አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ሀገር ገንዘቦችን በማተም እና የተለያዩ ማዕድናት በመያዝ ወንጀል የተጠረጠሩ የፀሃይ ሪል እስቴት ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ በዘጠኝ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ተደራራቢ ክስ ተመሰረተባቸው።
ክሱ የተመሰረተው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ልደታ ምድብ 8ኛ የገቢዎችና ጉሙሩክ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ክሱ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል 1ኛ የፀሐይ የሪል እስቴት መስራች፣ ባለድርሻ እና ሥራ አስኪያጅ ቺያን ኩዊን እንዲሁም በፀሐይ ሪል እስቴት ውስጥ በተለያዩ የኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ ሲሰሩ የነበሩ ቻን ዩቻንግ፣ ሊ ሳዩ፣ ሊ ሻን ሎንግ፣ ዚ ሀይ ሎንግ እና ጂን ባኦ ኩዋን ይገኙበታል።
የፍትህ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ የወንጀል ተሳትፎ ጠቅሶ ሰባት ተደራራቢ ክሶችን አቅርቦባቸዋል።
በወንጀል ህግ ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተከሳሾቹ ፀሀይ ሪል እስቴት ኃ/የተ/የግ/ማህበር ውስጥ 11ኛ ወለል ላይ በሚገኘው ቤት ውስጥ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በጋራ በመሆን፥ ከነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ/.ም እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ሀሰተኛ ገንዘብ ለመስራት የሚያገለግሉ መሳሪያዎች፣ የተለያዩ ኬሚካሎች እና ወረቀቶች በመጠቀም ሀሰተኛ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን፣ የአሜሪካ ዶላር፣ ዩሮ፣ የእንግሊዝ ፓውንድ ፣ የቻይና ዩዋን እና የሌሎች የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን አመሳስለው በማተም ላይ እያሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው በዐቃቤ ህግ ተጠቅሷል።
በሁለተኛው ክስ ደግሞ በእነዚሁ ተከሳሾች ላይ እንደቀረበው የወንጀል ህጉ ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተከሳሾቹ በሚኖሩበት እና በሚጠቀሙት መኖሪያ ቤት ውስጥ ገንዘቦች ለመስራት የሚያገለግሉ ፥ 2 የብር ማተሚያ ማሽን እና የተለያዩ ኬሚካሎች ማለትም በጀሪካን፣ በጠርሙስ፣ በብልቃጥ እና በበርሜል ባለ 500 ኖት ሀሰተኛ ዩሮ ለመስራት የተዘጋጀ በገንዘብ በ60 ሚሊየን 750 ሺህ ብር የሚገመት ነጭ ወረቀት ብዛት በነጠላ 121 ሺህ 500 ዩሮ እና 42 ሚሊየን 400 ሺህ ዶላር የሚገመት ሀሰተኛ ዶላር ለመስራት የተዘጋጀ ባለ 100 ኖት 424 ሺህ አረንጓዴ ወረቀት የተገኘባቸው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም 16 ሚሊየን 150 ሺህ የሚገመት ነጭ የዶላር ወረቀት ፣ የተለያየ ነጭ ዱቄት፣ አንዱ እሽግ በውስጡ 500 ወረቀት የያዘ 32 እሽግ በብር ቅርፅ የተቆራረጡ ወረቀቶች ፣ በአሉሙኒየም የተጠቀለለ በገንዘብ ቅርፅ የተቆረጠ ጥቁር ቀለም ያለው ወረቀት፣ 28 እሽግ አንዱ 500 የያዘ የገንዘብ መስሪያ ወረቀት እንዲሁም ገንዘብ ለመስራት የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ይዘው በፀጥታ አካላት በተደረገ ክትትል ይዘውት የተገኙ መሆኑን ዐቃቤ ህግ ጠቅሶ ሀሰተኛ ነገሮችን ለመስራት የሚያገለግሉ መስሪያ እና መሳሪያዎች መያዝ ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
3ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ ተከሳሸ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን በዚህም የወንጀል ህግ አንቀፅ 359 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ፥ ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገው ፍተሻ ሀሰተኛ የሆኑ ባለ 100 የገንዘብ ብዛቱ 297 ሺህ 400 የአሜሪካ ዶላር ፣ ባለ 50 የገንዘብ ብዛቱ 36 ሺህ 250 የእንግሊዝ ፓውንድ ፣ ባለ 500 62 ሺህ የሆነ ዩሮ፣ እና ባለ 200 65ዐ ሺህ 600 ዩሮ እንዲሁም ባለ 1 ሺህ 567 የቻይና ዩዋን ይዞ የተገኘ መሆኑ ተጠቅሶ ተከሳሹ ላይ ሀሰተኛ ገንዘብ ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።
በተጨማሪም በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የብሄራዊ ባንክ አዋጅን በመተላለፍ ተከሳሹ መኖሪያ ቤቱ እና በቢሮ በቀን በነሐሴ 25 እና በጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም በፀጥታ አካላት በተደረገ ብርበራ 1 ሺህ 245 የአሜሪካ ዶላር እና 200 የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ድርሃም ይዞ የተገኘ መሆኑ ተጠቅሶ፥ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በኩል የውጭ ሀገር ገንዘብ መመንዘርና የማዘዋወር ፍቃድ ሳይሰጠው የውጭ ሀገር ገንዘብ በህገወጥ መንገድ መያዝ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።
ይኸው አንደኛ ተከሳሽ በሌላ በቀረበበት 5ኛ ክስ ላይ ደግሞ ተከሳሹ ማዕድን የመያዝ ፍቃድ ሳይኖረው ክብደቱ 108 ነጥብ 43 እና 51 ነጥብ 88 ግራም የሚመዝን ኦፓል፣ 4 ነጥብ 99 የሚመዝን ኳርትዝ፣77 ነጥብ 71 የሚመዝን አጌት፣104 ነጥብ 59 የሚመዝን ማግኔታይት የተፈጥሮ ማዕድን ይዞ የተገኘ በመሆኑ የአዋጁን ድንጋጌዎች በመተላለፍ ወንጀል ተከሷል።
በተጨማሪም አንደኛ ተከሳሽ በኮንትሮባንድ ወንጀልም ሌላ ክስ ቀርቦበታል።
6ኛ ክስ ላይ ደግሞ ከ2ኛ እስከ 9ኛ ባሉት ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን፥ በዚህ ክስ ላይ እንደተመላከተው የፀና የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖረው በሀገር ውስጥ ሲኖር የተያዘ በመሆኑ በፈፀመው የፀና የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖር በሀገር ውስጥ መኖር ወንጀልም ተከሷል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ላይ የቀረበባቸው ተደራራቢ የወንጀል ክስን በችሎት እንዲደርሳቸው ተደርጎ ማንነታቸው ተረጋግጧል።
በዚህም ከ1 እስከ 6 ኛ የተጠቀሱ ተከሳሽ ጠበቆች የአንደኛ ተከሳሽ የልብ ህመምተኛ መሆናቸውንና ቋሚ አድራሻ እንዳላቸው ጠቅሰው የዋስትና መብት እንዲፈቀድ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ከ2 እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ደንበኞቻቸውን በሚመለከት የቀረበባቸው ክስ ከ7 ዓመት በላይ በማያስቀጣ የወንጀል ድንጋጌ መከሰሳቸውን ጠቅሰው የዋስትና መብት ጥያቄ አንስተዋል።
ዐቃቤ ህግ ደግሞ ተከሳሾቹ ተደራራቢ ክስ የቀረበባቸው እና ቋሚ አድራሻ የሌላቸው ከመሆኑ አንጻር ቢወጡ የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ሊቀርቡ አይችሉም ሲል በመቃወም ተከራክሯል።
የሰበር ሰሚ ችሎት ተደራራቢ ክሶችን በሚመለከት በልዩነት ዋስትናን ሊያስከለክል ስለሚችሉ ድንጋጌዎች በማብራራት በመከራከር ተጠርጣሪዎቹ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ጠይቋል።
የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ችሎቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን ተከሳሾቹም እስከ ቀጠሮ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ አዟል።
በታሪክ አዱኛ