አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 16 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመሬት ኃብት አስተዳደር የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማስቆም ቅንጅታዊ አሰራርን ማስፋት እንደሚገባ የፌደራል የሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ በመሬት ዘርፍ የሚስተዋሉ የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ነው።
የፌደራል የሥነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፥ ሙስና የሀገርን ሰላምና ልማት እያደናቀፈ የሚገኝ አደገኛ ወንጀል ነው።
የሙስና ወንጀል እንቅስቃሴን በመታገል የሕዝብ ኃብት ለሀገር ልማት እንዲውል ለማድረግ የአመራሩን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅም ገልጸዋል።
ሙስናን የመታገል እንቅስቃሴ በማስፋት ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የሀገርን ኃብት ሌቦች እንዳሻቸው እንዲጠቀሙበት ባለመፍቀድ ለዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ብልጽግና እንዲውል በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን በበኩላቸው÷ መሬትን በተገቢው መንገድ በማስተዳደር ለዜጎች ፍትኃዊ ተጠቃሚነትና ለሀገር ልማት እንዲውል ማድረግ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።