አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል መስተዳድር ም/ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የእሳት አደጋ ተጎጂዎችን ማቋቋምን ጨምሮ የተለያዩ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ።
ም/ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ጳጉሜ 1 ቀን 2015 ዓ.ም በተከሰተው የእሳት አደጋ የደረሰው የንብረት ጉዳት መጠን፣ ተጎጂዎች ልየታና ጉዳት የደረሰባቸውን መልሶ ለማቋቋም የተመሰረተው ኮሚቴ በሰራቸው ስራዎች ዙሪያ ተወያይቷል።
በዚህም በ49 የንግድ ሱቆች ሲሰሩ የነበሩ ነጋዴዎች የገንዘብና የአይነት ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልፆል።
የእሳት አደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ መረጃዎች ተሰብስበው ለፎረንሲክ ምርመራ ተልኮ ውጤት እየተጠበቀ እንደሆነም ተጠቁሟል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ ስራዎችን በቅንጅት በመስራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጎጂዎችን በደረሰባቸው ጉዳት መጠን የመደገፍ ስራ ይሰራል ብለዋል።
በህጋዊነት እየሰሩ ለነበሩ ተጎጂዎች ምትክ የመስሪያ ቦታ ማመቻቸት በፍጥነት እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ደረጃውን የጠበቀ የገበያ ማዕከል በማህበር ተደራጅተው ለሚገነቡ አካላት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር አስታውቀዋል።
መስተዳድር ም/ቤቱ ከእሳት አደጋ ተጎጂዎች መልሶ ማቋቋም በተጨማሪ በ26ኛው ዓለም አቀፍ የሀረሪ ባህልና ስፖርት ፌስቲቫል በዓል አከባበር ላይ በሚተገበሩ ስራዎች ዙሪያ በመወያየት አቅጣጫ አስቀምጧል።
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ጀጎል ቅርስ ዙሪያ፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በፅዳትና ውበት የተከናወኑ ስራዎችን በማስፋት ጀጎልን ለነዋሪዎችና ለቱሪስቶች ምቹና ማራኪ የማድረግ ስራ ላይ ምክር ቤቱ ተወያይቷል።
በተሾመ ኃይሉ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!