አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የ2023 “ስታርትአፕ” ሽልማት የአፍሪካ ጉባዔ የታለመለትን ግብ ማሳካቱን የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡
ወ/ሮ ሙፈሪሃት ከዓለም አቀፉ “ስታርትአፕ” ሽልማት አዘጋጆች ጋር በጉባዔው አፈፃፀም ላይ መክረዋል፡፡
በውይይታቸውም ጉባዔው÷ በአፍሪካ የመንግሥትና የኢንዱስትሪ አመራሮች፣ የዘርፉ ባለድርሻና አጋር አካላት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች (ስታርትአፖች)፣ የቴክኖሎጂና ሥራ ፈጠራ ምኅዳሩ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸውን አካላት በአንድ መድረክ ያገናኘ መሆኑ ተነስቷል፡፡
እንዲሁም ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ተገቢውን የክኅሎት፣ የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂና የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር ችሏል ነው የተባለው ጉባዔው፡፡
የግሎባል ኢኖቬሽን ኢኒሼቲቭ ግሩፕ መሥራችና እና የጉባዔው አዘጋጆች በበኩላቸው÷ “በኢትዮጵያ በነበረን ቆይታ ደስተኞች ነን” ማለታቸውን የሥራና ክኅሎት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡