አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
አቶ ኦርዲን በአባድር ወረዳ ለሚገነባው ዘመናዊ ጤና ጣቢያ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት እንደገለጹት÷ የጤና ጣቢያው መገንባት የአካባቢው ነዋሪ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል።
በጁገል ዙርያ የሚገነባው ዘመናዊ ጤና ጣቢያ ፕሮጀክት የዩኔስኮን መሰረታዊ የግንባታ ሥርዓትን እና ባሕላዊ ዕሴትን በጠበቀ መልኩ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቱ መገንባት የሕብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ያሳልጣል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሂ÷ በተያዘው በጀት ዓመት የጤናውን ዘርፍ ለማጎልበት፣ የማኅበረሰቡን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እርካታና ጥራትን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
የአባድር ጤና ጣቢያ በታቀደለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት፡፡