Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሀገር በቀል ዕውቀቶች የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 17 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለቱሪዝም መስህብነት በማዋል የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
በየዓመቱ ጥቅምት 17 ቀን የሚካሄደው የየም ብሔረሰብ ባህላዊ መድኃኒት ለቀማ (ሳሞታ-የከረመ መድኃኒት) ዛሬ ተከናውኗል።
ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በሚነገርለት የየም ብሔረሰብ ሀገር በቀል እውቀት በሆነው ባህላዊ መድኃኒት ለቀማ፥ ከልጅ እስከ አዋቂ በነቂስ ወጥቶ በህብረት የመልቀምና የእውቀት ሽግግር የሚደረግበት ዕለት ነው።
የየም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ሞጋ እንዳሉት፥ የየም ብሔረሰብ ባህላዊ መድኃኒት ለቀማን በተመድ የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) አስመዝግቦ ለዓለም ማህበረሰብ በማስተዋወቅ ከዘርፉ የዞኑን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።
በዓመት አንድ ቀን የሚከወነው ባህላዊ መድኃኒት ለቀማ ለዓመት የሚያገለግል ነው ያሉት ኃላፊው፥ ቦር ተብሎ በሚጠራው ተራራ አካባቢ የሚከናወን መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህ ስፍራ በተራራው የመጀመሪያውን የማለዳ ፀሀይ ቀድሞ የሚያገኝ በመሆኑና በዚሁ አካባቢ የሚፀድቁ ዕፅዋት በሽታን ለመከላከልና ፈዋሽነት አቅም አላቸው ተብሎ ስለሚታመን ለለቀማ መመረጡንም ነው የተናገሩት።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሰለሞን አሊዩ በበኩላቸው፥ የማህበረሰቡን ማንነት ገላጭ የሆነውን ሀገር በቀል እውቀት በማስተዋወቅና ለቱሪዝን መስህብነት በማዋል የገቢ ምንጭ እንዲሆን እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በዛሬው እለት የየም ብሔረሰብ ባህላዊ መድኃኒት ለቀማ (ሳሞታ ከራሚ መድኃኒት) ቅመማና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተመርቋል።
በተስፋሁን ከበደ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version