Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ 3 ሠራተኞችን ለህልፈት የዳረገው የሪል ስቴት ሕንጻ ግንባታ ሥራ እንዲቆም ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ባሳለፍነው ዓርብ የሪል ስቴት ሕንጻ ግንባታ ሥራ ላይ የነበሩ 3 ሠራተኞች ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ የሕንጻው ግንባታ እንዲቆም መደረጉን የከተማዋ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ዴሲሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ ባሳለፍነው ዓርብ በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በጅምር ግንባታ ላይ የሚገኝ ባለ 9 ወለል የአርሂቡ ሪል ስቴት ሕንጻ ግንባታ ሥራ ላይ የነበሩ 3 ሠራተኞች ሕይወት አልፏል፡፡

ሠራተኞቹ ሲሚንቶ ወደ ላይ የሚያወጡበት ጋሪ የተሸከመው የብረት ገመድ በመታጠፉ የብረት ገመዱን ለማስተካከል በእጃቸው ይዘው በሚያንቀሳቅሱበት ወቅት በአቅራቢያው ከነበረ የኤሌክትሪክ ገመድ ጋር በመገናኘቱ ከሕንጻው ወደ መሬት ወድቀው ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

ተጨማሪ አንድ ሰራተኛ ወደ ሕክምናተቋም መወሰዱን ያብራሩት አቶ ገዛኸኝ÷ሶስቱ ሠራተኞች ግን ወዲያውኑ ሕወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

የደረሰውን አደጋ ተከትሎም ሕንጻው የግንባታ እንቅስቃሴውን እንዲያቆም መደረጉን ነው ያስታወቁት፡፡

ከዚህ ባለፈም የሕንጻው ባለቤት፣ የአማካሪውንና የተቋራጩን የግንባታ ፈቃድ በመያዝ ከአደጋው ጋር በተያያዘ ማብራሪያ እንዲሰጡ መታዘዛቸውን ገልጸዋል።

በሕንጻ አዋጅና መመሪያ መሰረት ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመው÷ለጠፋው ሕይወትም በሕግ እንደሚጠየቁ አክለዋል ፡፡

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version