አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን መስፈርቱን በማሟላት በሀገሩ ሜዳ ጨዋታውን እንዲያደርግ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለጹ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እያካሄደ ነው፡፡
እግር ኳስ በኢትዮጵያ ካለው ሕዝባዊ መሰረት ባሻገር በዓለም አቀፍ መድረክ ለገጽታ ግንባታና በስፖርት ዲፕሎማሲ ከሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሣደግ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ሲሉ አምባሳደር መስፍን በጉባዔው ላይ ተናግረዋል፡፡
እግር ኳስ ፌዴሬሽን በእግር ኳስ ልማትና ከሌሎች ሀገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ትብብር ለመፍጠር የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በእግር ኳስ በዓለምና በአኅጉር አቀፍ መድረክ ውጤት ለማስመዝገብ እንድትችል ፌዴሬሽኑ በትኩረት መሥራት እንዳለበትም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስፈርትን ያሟላ ስታዲየም በማዘጋጀት የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በሜዳው እንዲጫወት በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው÷ የፊፋ እና ካፍ መስፈርት ያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ለእግር ኳስ ልማት መዋል ያለበት ወጪ ለውጭ ሀገራት ጉዞና ተያያዥ ወጪ እየዋለበመሆኑ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ፌዴሬሽኑ በታዳጊዎችና ሴቶች የእግር ኳስ ልማት ላይ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
የክለቦች ፈቃድ አሰጣጥ አሠራርን ወደ ሥራ ለማስገባት እንዲሁም ተቋርጦ የነበረውና በድጋሚ የተጀመረው የካፍ ሲ እና ዲ ላይሰንስ ስልጠና እንደሚቀጥል መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በጉባዔው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የማሟያ ምርጫ እንደሚከናወንም ተጠቁሟል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!