Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አሜሪካ በሃማስ እና እስራኤል መካከል ተኩስ አቁም እንዲደረግ የቀረበውን ጥሪ ውድቅ አደረገች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በሃማስ እና በእስራኤል መካከል ተኩስ አቁም እንዲደረግ የቀረበውን ዓለም አቀፋዊ ጥሪ እንደማትቀበል አስታወቀች፡፡

የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኬርቢ፥ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ተኩስ አቁም ይደረግ ለማለት ትክክለኛው ሰዓት አይደለም ብለዋል።

ከተኩስ አቁም ይልቅ ወደ ጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ጦርነቱን “ጋብ ማድረግ” የተሻለ አማራጭ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ በጋዛ ለሚኖሩ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ይነገራል።

ቃል አቀባዩ ተጨማሪ የእርዳታ መኪኖች በግብፅ በኩል እንደሚገቡ እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

አያይዘውም ዋሺንግተን በየቀኑ ሰብአዊ ድጋፍ ጭነው ወደ ጋዛ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ወደ 100 እንዲጨምር ከእስራኤል ጋር መነጋገሯንም አስረድተዋል።

ባለፈው እሁድ 45 ሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በግብጽ ራፋ ድንበር በኩል ወደ ጋዛ መግባታቸውን ያነሱት ቃል አቀባዩ ይህ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ እና ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

እስራኤል በበኩሏ “ሃማስ እስከሚጠፋ ድረስ ተኩስ አቁም የሚባል ነገር የለም” በሚል አቋሟ እንደፀናች መሆኑን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም “ተኩስ አቁም ይደረስ ማለት እስራኤልን ለሃማስ እጅሽን ስጭ እንደማለት ነው፤ ይህ መቸም አይሆንም” ሲሉ ተደምጠዋል።

በእስራኤል ሃማስ ግጭት ሳቢያ እስካሁን 8 ሺህ 300 ፍልስጤማውያን በጋዛ ለህልፈት ሲዳረጉ 1 ሺህ 400 እስራኤላውያን በጦርነቱ ሰለባ መሆናቸውን መረጃ ዎች ያመላክታሉ።

Exit mobile version