አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከጣሊያን የተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ልዑካን ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከጣልያን ከበርጋሞ ከተማ ከንቲባ ጆርጂዮ ጎሪን ፣ ከቤርጋሞ ዩኒቨርሲቲ ሬክተር ሰርጂዮ ካቫሊየሪ(ፕ/ር) ፣ የኢንዱስትሪና የምርምር ተቋማት ኃላፊዎች እና ከልዩ ልዩ ተቋማት የተውጣጡ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር ነው የተወያዩት።
በውይይታቸውም ÷ በሁለቱ ሀገራት የነበረውን መልካም ግንኙነትና ትብብር በማጠናከር በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር፣ በሰው ሀይል ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፎች በጋራ መስራት በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ መክረዋል።
በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ጣልያን በቴክኖሎጂ ያደገች ሀገር በመሆኗ ኢትዮጵያ ብዙ የምትወስዳቸው ልምዶችና ተሞክሮዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
በዚህም በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር እንዲሁም በዲጂታላይዝሽን ላይ አብረው መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያልተነካ እምቅ አቅም ያላት ሀገር እንደመሆኗ የጣሊያን ኩባንያዎች በስፋት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ማስረዳታቸውን ከሚኒስተሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ልኡካን ቡድኑም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነትና ትብብር በማጠናከር በኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በአይ ሲ ቲ ፓርክ፣ በዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሰው ሀይል ግንባታ፣ በጥናትና ምርምር እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እንዲሁም ተቋማዊ አቅም ግንባታ ላይ ተባብረው መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡