አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ያለውን የወርቅ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ።
የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት የሦስት ወራት ዕቅድ ክንውን አፈፃፀምና የቀጣይ ዕቅድ ዙሪያ በዲማ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው።
አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በውይይቱ ላይ በክልሉ ሕገ-ወጥ የወርቅ ዝውውርን በመቆጣጠር ሀብቱን ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
ከክልሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ ማዕድን መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱንም አንስተው፤ የዘርፉን ተግዳሮቶች በመቅረፍ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባውን የወርቅ መጠን ማሳደግ ይገባል ማታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ የባለድርሻ አካላት የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በማጠናከር ሕገ-ወጥ የወርቅ ዝውውርን ለማስቆም በትኩረት እንዲሠሩም ነው ያሳሰቡት፡፡
በወርቅ ምርት ሥራና ቁጥጥር ላይ የወረዳና የዞን አመራሮች በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ዋና ዳይሬክተር አኳታ ቻም ባቀረቡት ሪፖርት በክልሉ ሕገ-ወጥ የወርቅ ዝውውር በመበራከቱ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ መጠን መቀነሱ ተመላክቷል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት 312 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ታቅዶ የገባው 63 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም ብቻ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
አፈፃፀሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ31 ነጥብ 54 ኪሎ ግራም ብልጫ ቢኖረውም ከተያዘው ዕቅድ አንፃር ዝቅተኛ በመሆኑ የባለድርሻ አካላትን ርብርብ እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል፡፡
በጋምቤላ ክልል የወርቅ ማዕድን ከሚመረትባቸው መካከል የዲማ፣ የአቦቦ፣ የጋምቤላና የመንገሺ ወረዳዎች ይገኙበታል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!