Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ የአሠራር ሥርዓት እየተዘጋጀ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ወደ ቀደመ ፍትሕ የማረጋገጥ ሥራ እንዲገቡ የአሠራር ሥርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አያሌው አባተ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ማሕበረሰባዊ መሠረት ያላቸው ቢሆኑም አስተዋጾአቸው እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

በማህበረሰቡ ተቀባይነት ያገኙና የሚተገበሩ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶችን መተግበር ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡

ሕግ ሀገርን የመሥራት እና ማህበረሰብንም የማነጽ አቅም እንዳለው ተናግረው፤ መሠረታዊ የወንጀል ሕግ ላይ የተቀመጡ የማይነኩ መርሆዎችን ሳይጥስ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ተቋማትን በሕግ እውቅና በመሥጠት ፍትሕን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል፡፡

ለሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ተቋማት በውይይቶች ላይ ከማሳተፍ ባለፈ በተፈለገው መንገድ ድጋፍ ሲደረግላቸው እንዳልነበርም አስታውሰዋል፡፡

ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች በማኅበረሰቡ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች ላይ የቆሙ በመሆናቸው በተገልጋዮች ዘንድ ቅቡል ናቸው ተብሏል።

የሚከሰቱ አለመግባባቶችንና ቅራኔዎችን የመፍታት አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ የጸጥታ ችግሮች ሲፈጠሩ በማብረድ፣ የግጭቶችን መነሻ ቀድሞ በመለየትና በመከላከል ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑንም አሚኮ ዘግቧል፡፡

ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት በቀላሉ ተደራሽ ባልሆነባቸው ገጠራማው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላምን በማስፈን ሚናቸው የጎላ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በሕቡዕ ተፈጽመው በመደበኛ ፍትሕ ሥርዓቱ መፍትሔ ያላገኙ ችግሮችን ጭምር በመለየት አጥፊውን በመቅጣትና ተበዳዩን በመካስ ሚናቸው የጎላ ነው ተብሏል፡፡

 

 

 

Exit mobile version