አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ የኮሪያዋ ቹንቾን ከተማ ከንቲባ ዮክ ቶንግ ሃን የኢትዮጵያን እና ደቡብ ኮሪያን ግንኙነት በሚያጠናክር መልኩ ከአዲስ አቨበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በወጣቶችና ተማሪዎች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ።
የአዲስ አበባና የደቡብ የኮሪያ ቹንቾን ከተማ እህትማማችነት 20ኛ ዓመት በዓል ግንኙነታቸውን በይበልጥ በሚያጠናክሩ መርሐ-ግብሮች እየታሰበ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሃንግ ሶክሂ፣ የቹንቾን ከተማ ከንቲባ ዮክ ቶንግ ሃን እና ሌሎችም የልዑኩ አባላት በደጃዝማች ወንድይራድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርት ቤት በመገኘት በወጣቶችና ተማሪዎች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ጉብኝት አድርገዋል፡፡
አምባሳደር ሃንግ ሶክሂ በጉብኝቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ 70 ዓመታትን የተሻገረ ግንኙነት እንዳላቸው አውስተዋል፡፡
ግንኙነቱ ኢትዮጵያውያን የቃኘው ሻለቃ የጦር ኃይል አባላት ለኮሪያ ሁለንተናዊ ነጻነት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ መነሻ በማድረግ በፈረንጆች 1963 የተጀመረ መሆኑንም ነው ያስታወሱት፡፡
ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ለደቡብ ኮሪያ ነጻነት የከፈሉትን የሕይወት ዋጋ መቼም የምንረሳው አይሆንም ያሉት አምባሳደሩ÷ ደቡብ ኮሪያ ከዚያን ወቅት አንስቶ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመደገፍ በሁሉም ረገድ ዘርፈ ብዙ ጥረት እያደረገች ትገኛለች ብለዋል።
ከንቲባ ዮክ ቶንግ ሃን በበኩላቸው÷ የሁለቱን ሀገራትና ከተሞች ግንኘነት በሚያጠናክር መልኩ ወጣቶችና ተማሪዎች ለይ በጋራ እንሠራለን ማለታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ትምሕርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
ይህም ትብብር በትምሕርት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ረገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትምሕርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወንድሙ ኡመር የኢትዮጵያና የደቡብ ኮሪያ ግንኙነት በደም የተሳሰረ ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሰው፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ዘርፍ ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተጨባጭ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለአብነት የተማሪዎች የምገባ መርሐ-ግብርና የትምሕርት ቤት የደንብ ልብስ አቅርቦትን ጠቅሰዋል፡፡
ከእህት የቹንቾን ከተማ ጋር ለሁለቱም ከተሞች ዘላቂ ዕድገት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የደቡብ ኮሪያ ቾንቹን ከተማ ከንቲባ ዮክ ቶንግ ሃን በአዲስ አበባ ከተማ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ለአብርኾት ቤተ- መፃሕፍት ላደረጉት ድጋፍ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!