Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጉቦ ለውጭ ዜጎች ፓስፖርት በመስጠት፣ ዜጎችን በህገወጥ መንገድ ከሀገር በማስወጣት ወንጀል የተጠረጠሩ 28 ግለሰቦች ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከደላላ ጋር በመመሳጠር ከህግ ውጪ በጉቦ ለውጭ ዜጎች ፓስፖርት በመስጠት፣ ዜጎችን በህገወጥ መንገድ ከሀገር በማስወጣት ወንጀል የተጠረጠሩ 28 ግለሰቦች ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ተጠርጣሪዎቹን በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ያቀረበው የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ከዚህ በፊት በተሰጠው የ14 ቀን ጊዜ ውስጥ የሰራውን የምርመራ ውጤት ለችሎቱ አቅርቧል።

በጠበቆች በኩል በፖሊስ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ላይ የመቃወሚያ የመከራከሪያ ነጥቦች ቀርበው ክርክር ተደርጓል።

ተጠርጣሪዎቹ የቀድሞ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ገምበታ፣ ምክትል ዳይሬክተር ቴድሮስ ቦጋለን ጨምሮ 28 ግለሰቦች ሲሆኑ ከነዚህ መካከል አራቱ ሴቶች ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዘርፍ መርማሪ ከዚህ በፊት በተሰጠው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ የ16 ሰው ምስክር ቃል መቀበሉን ገልጿል።

የ27 ተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበሉንና 8 ባንኮች እና ለተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ማስረጃ እንዲሰጠው መጠየቁን አብራርቷል።

ቀሪ ስራዎችን የኦዲት የምርመራ ውጤት፣ የተጨማሪ ምስክር ቃል መቀበል፣ ከባንኮችና ከተቋማት ማስረጃ መሰብሰብ ስራ እንደሚቀረው ገልጾ፤ ተጨማሪ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ላይ በምስክርነት የተለዩ ግለሰቦች ማስፈራራያ ዛቻ ስጋት እንዳለባቸው ጥቆማ እንደደረሰው ጠቁሞ፤ ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ምስክር ሊያስፈራሩ ይችላሉ በማለት ስጋቱን ገልጿል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው በደንበኞቻቸው ላይ ፖሊስ ያቀረበው የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ምክንያቶች ተጠርጣሪዎችን አስሮ ለማቆየት የሚያስችል አይደለም በማለት ተከራክረዋል።

የወንጀል ተሳትፏቸው ተለይቶ ከስራ መዘርዝራቸው ጋር ባልቀረበበት ሁኔታ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁ አግባብ አይደለም በማለት ተከራክረዋል።

በፍርድ ቤቱ በኩልም ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን የወንጀል ተሳትፏቸውን እንዲያብራራ ተጠይቋል።
መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ አንደኛ ተጠርጣሪን በሚመለከት በህገወጥ መንገድ የሰዎች ዝውውር፣ የቪዛ ጊዜያቸው ያለቀባቸው የውጭ ሀገር ዜጎችን መፈጸም የነበረባቸው የዶላር ክፍያን ለራስ ጥቅም በማዋል በብር እንዲከፍሉ ማድረግ ወንጀል፣ የሶስት ወር ፍቃድ ይዘው የመጡ የውጭ ዜጎችን የአንድ ዓመት ፍቃድ ይዘው እንደመጡ ማድረግ ወንጀል እንዲሁም ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለውጭ ሀገር ስራ ስልጠና ወስደው ከተላኩ 400 ግለሰቦች ጋር ሌላ 100 ግለሰቦችን ቀላቅሎ ወደውጭ በመላክ የወንጀል ደረጃ ጥቆማ እንደደረሰውና ተሳትፎ እንዳላቸው የምርመራ ማጣሪያ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሷል።

ከድር የተባሉ 3ኛ ተጠርጣሪን በሚመለከትም በ3 ጊዜ ገደብ እንዲሰጡ የተወሰነ በስቶር የተቀመጠ ፓስፖርቶችን ለሚገባው ሰው መስጠት ሲገባ 3 ወር በማሳለፍ ሰዎች ተጨማሪ ገንዘብ ከፍለው እንዲወስዱ በማድረግ ህገወጥ ተግባር ተሳትፎ እንዳላቸው መጠርጠራቸውን ገልጾ አብራርቷል።

በሌላ በኩል 27ኛ ተጠርጣሪ የተቋሙ ሰራተኛ ባልሆኑበት ሁኔታ ያለአግባብ የኢንቨስትመንት መሬት ለመውሰድ በሄዱበት መንገድ ላይ ነው የተያዙት ስለማይፈልጓቸው ቃላቸውን አልተቀበሉም ስለዚህ በዋስ ሊለቀቁ ይገባል የሚል መከራከሪያን በሚመለከት ፖሊስ ግለሰቡ ከተቋሙ ውጭ ሰው በመደለል ከውስጥ ካለ ሰው ጋር በድለላ በማገናኘት ስራ የተሰማሩ እንደሆኑ ጠቆሶ መልስ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ለአልሸባብ አባላት ጭምር በህገወጥ መንገድ በገንዘብ ፓስፖርት በመስጠት ተሳትፎ አላቸው ያላቸው ተጠርጣሪዎችንም ፖሊስ ጠቅሷል።

የተወሰኑትን የወንጀል ተሳትፎ በመግለጽ ከምርመራ ስፋት ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር የተቀሩትን ተጠርጣሪዎች ተሳትፎ ከመዝገቡ ጋር ማያያዙንም ጠቁሟል።

23ኛ ተጠርጣሪ የስራ ድርሻዬ ከፓስፖርት ጋር ግንኙነት የለውም በማለት በፖሊስ ቃሌን እንድሰጥ የተደረኩት ከሸኔ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት አለህ ተብዬ ነው በማለት የተጠረጠሩበት ወንጀል እንደማይመለከታቸው ጠቅሰው ተከራክረዋል።

በፖሊስ በበኩሉ 23ኛ ተጠርጣሪ ለሸኔ የሽብር ቡድን አባላት ፓስፖርት በማመቻቸት፣ ከስራ ገበታው በመጥፋትና ተመልሶ በመምጣት ላይ እንደነበር በመግለጽ የወንጀል ተሳትፎ እንዳለው በማብራራት መልስ ሰጥቷል።

በአጠቃላይ ጠበቆች በፖሊስ የቀረቡት ጥቆማዎች ናቸው በማለት የቀረበው ጥቆማን ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮ አካል አድርጎ ሊመለከት አይገባውም በማለት የፖሊስ ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ጠበቆቹ በፖሊስ የቀረበው ተጨማሪ ጊዜ ደንበኞቻቸውን በእስር ሊያቆይ የሚችል በቂ ምክንያት የሌለው መሆኑን በመግለጽ ለተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲፈቀድ ጠይቀዋል።

የስራ መዘርዝራቸው አጠቃላይ ተሳትፏቸውን ችሎቱ ከምርመራ መዝገቡ እንዲመለከትላቸው ጠይቀዋል።

አጠቃላይ የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እና ክርክሩን መርምሮ ተገቢ ትዕዛዝ ለመስጠት በይደር ለነገ ከሰዓት ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version