Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 37ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን እና 44ኛውን የአስፈጻሚ ምክርቤት ስብሰባ ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅት እተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለፁ፡፡

በመጭው የካቲት ወር በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የአፍሪካ ኀብረት የአስፈፃሚ  ምክር ቤት ስብሰባ እና የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባዔ ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ከተለያዩ ተቋማት ከተወከሉ የብሔራዊ ኮሚቴው አባላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።

የዝግጅቱ  ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ÷ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲናና የአፍሪካ ኀብረት መቀመጫ መሆኑኗን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በየዓመቱ የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባዎች ታስተናግዳለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ÷ ሁነቱን በላቀ ደረጃ ለማዘጋጀት ከ22 በላይ ተቋማት አባል የሆኑበት የዝግጅት ብሔራዊ ኮሚቴ መዋቅሩን ገልፀዋል።

ይህን ዕቅድ ለማሳካት በዋናነት ኃላፊነቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሆንም ሁነቱን በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ከተለያዩ የፌደራል ተቋማት እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በውይይቱ ባለፈው ዓመት የነበሩ ስኬታማ ተግባሮች እና ክፍተቶች ተለይተው ለውይይት የቀረበ ሲሆን ፥የኢትዮጵያን ተደማጭነትና የመሪነት ሚና ለማስቀጠል እንዲሁም የኢኮኖሚ ማዕከልነት ለማጠናከር በልዩ ትጋት መስራት እንደሚገባም ነው ያሳሰበው፡፡

የኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስራ ስኬቶች መገለጫ አንዱ የሆነውን የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባዔ  ከሀገራዊ ጠቀሜታ አንፃር በመረዳት ሁሉም በየመስኩ ለስኬቱ አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version