አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ ፓርላማዎች ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለፁ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ከደቡብ ኮሪያ የፓርላማ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ የኮሪያ የፓርላማ አባላት ኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ 60 ዓመት የዘለቀ ግንኙነት እንዳላቸው ገልፀው ፥ ይህንኑ የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎችን እየተሰሩ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ሁለቱ ሀገራት ያላቸው ዘመናትን የዘለቀ ግንኙነት በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡
ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እየሰሩ መሆናቸውንና የሁለቱ ሀገራት ምክር ቤቶች በልምድ ልውውጥና አብሮ በመስራት ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንዳለባቸውም ነው ያስረዱት፡፡
የኢትዮጵያ ፓርላማ የኢትዮ-ኮርያ ፓርላሜንታዊ ወዳጅነት ቡድን አዋቅሮ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢው ÷ የኮሪያ ሪፐብሊክም ተመሳሳይ ትኩረት በመስጠት ለሀገራቱ ግንኙነት የበኩሉን እንዲወጣ መጠየቃቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡