Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሆላ ሀውሲንግ ሶሉሽንስ ሪል እስቴት ከ8 ሚሊየን ብር ባልበለጠ ዋጋ ዘመናዊ ቤቶችን መገንባት ጀመረ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሆላ ሀውሲንግ ሶሉሽንስ የተሰኘው የሪልእስቴት ኩባንያ ከ8 ሚሊየን ብር ባልበለጠ ዋጋ ዘመናዊ ቤቶችን መገንባት መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ነብዩ ዳንኤል÷ ኩባንያው በአዲስ አበባ ከተማ በሜክሲኮ፣ ጎተራ፣ ባልደራስ፣ ቡልቡላ፣ ሃያሁለት እና ሌሎችም ሳይቶች የግንባታ ስራውን ያከናውናል ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች በፍጥነት እንደሚገነባም አስታውቀዋል፡፡

የድርጅቱ ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ዳግማዊ ጌታቸው በበኩላቸው÷ ሆላ ሃውሲንግ ሶሉሽን ከ8 ሚሊየን ብር በታች በሆነ ወጪ ቤቶቹን ከሁለት ዓመት ተኩል ባነሰ ጊዜ ገንብቶ ለደንበኞቹ እንደሚያስተላልፍ ገልጸዋል፡፡

ደንበኞች የኩባንያው ባለቤት መሆን አልያም ቤቱን ብቻ መግዛት እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

ሆላ ሀውሲንግ ሶሉሽን በተለይም ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ ከግሎባል ባንክ ጋር ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን÷ የመድን ሽፋኑን ደግሞ ከሉሲ ኢንሹራንስ ጋር መፈራረሙ ነው የተገለፀው፡፡

በስምምነቱም ከሆላ ሪልእስቴት ደንበኞች ጋር በተያያዘ ግሎባል ባንክ እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ረጅም ጊዜ አስፈላጊውን የፋይናንስ ብድር እንደሚያቀርብ ተጠቁሟል፡፡

በዚህም ደንበኞች በ1 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ቅድሚያ ክፍያ እንዲሁም በግንባታው ማስጀመሪያ ወቅት 1 ነጥብ 18 ሚሊየን ብር መክፈል የሚጠበቅባቸው ሲሆን÷ ቀሪውን ከ15 እስከ 25 ዓመታት በሚቆይ በዝቅተኛ ወለድ የባንክ ብድር አማካኝነት የቤት ባለቤት መሆን ይችላሉ ተብሏል።

Exit mobile version