አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሦስት ወራት ሙስናን ለመከላከል በተሰራው ሥራ ከ126 ሚሊየን ብር በላይ ሃብት ከብክነት መታደግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጀማል ረዲ እንዳሉት÷ በሩብ ዓመቱ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ የማስጨበጫ ሥልጠናዎች ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሰጥተዋል።
ከኅብረተሰብ የሚመጡ ጥቆማዎችን ትክክለኛነት በማጣራት አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ይህን ተከትሎም በሩብ ዓመቱ በተከናወኑ አስቸኳይ የሙስናን መከላከል ሥራ ከ126 ሚሊየን ብር በላይ የሕዝብና የመንግሥት ሃብትን ከብክነት መታደግ ተችሏል ነው ያሉት።
ከሙስና ወንጀሎች ጋር በተያያዘም ከ16 ሰዎች በላይ በቁጥጥር ሥር ኢንዲውሉ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
በ39 ተቋማት ላይ የሙስና ተጋላጭነትና አሰራር ሥርዓት ለመፈተሽ የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የዳሰሳ ጥናት ሲጠናቀቅ የመፍትሄ ኃሳብ በማስቀመጥ ተቋማት ተገቢውን ማስተካከያ እንዲያደርጉ ያግዛል መባሉንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡