Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሙስና ወንጀል የተከሰሱ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት 3 ሰራተኞች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተሰጠ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሲሚንቶ ግዢ ጋር ተያይዞ በሙስና ወንጀል የተከሰሱት የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽንና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ደሜን ጨምሮ 3 ግለሰቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተሰጠ።

ፍርድ ቤቱ በሰጠው የቅጣት ውሳኔን በሚመለከት በዐቃቤ ህግ በኩል ግን ይግባኝ ለማቅረብ የውሳኔ ግልባጭ ተጠይቋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ስም 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ከሁለት ፋብሪካዎች ገዝተው ለግለሰቦች በመሸጥ በመንግስት ላይ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል በማለት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተቋም የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተርን ጨምሮ በአራት ሰራተኞች ላይ ታህሳስ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸው ነበር።

በአጠቃላይ ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር ምንም አይነት የግዢ ፍላጎት ሳይኖር በአገልግሎቱ ስም በፃፏቸው ደብዳቤዎች ከዳንጎቴ እና ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በድምሩ 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ በመግዛት ወደ ተቋሙ ገቢ ሳያደርጉ ገበያ ላይ በመሸጥ 30 ሚሊየን 99 ሺህ 360 ብር ጥቅም ያገኙ መሆኑን ጠቀሶ ነበር ዐቃቤ ህግ ክስ ያቀረበው።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸውና በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ሶስት ምስክሮችን እና በተያያዥ የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርቧል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የምስክር ቃል መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ነበር።

ሆኖም ተከሳሾቹ በተለያዩ ቀናቶች ያቀረቡትን የመከላከያ ማስረጃ የመረመረው ፍርድ ቤቱ 1ኛ ተከሳሽን የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተቋም የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ ደሜ፣ በተቋሙ የግዢ ባለሙያ ናቸው የተባሉ ቱጅባ ቀልቤሳ እና ሙስጠፋ ሙሳን በተከሰሱበት ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

ከተሳሾቹ ጋር ቀደም ብሎ ክስ ቀርቦባቸው የነበረና ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ በችሎቱ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ የነበረው በተቋሙ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ግዢ ፋይናንስ ክፍል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ተስፋዬ የዐቃቤ ህግ ማስረጃን በተገቢው ተከላክለዋል በማለት በነጻ አሰናብቷቸው ነበር።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት ማቅለያና የቅጣት የማክበጃ አስተያየቶችን መርምሮ ተከሳሾቹ ጥፋተኛ በተባሉበት አንቀጽ 1ኛ ተከሳሽን በ2 አመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የወሰነ ሲሆን÷ ቀሪ ተከሳሾችን ደግሞ 1 አመት ከ6 ወራት እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

ዐቃቤ ህግ ከሁለት ፋብሪካዎች ያለአግባብ በተፈጸመ የ29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ግዢ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት ደርሷል ብሎ ክስ ያቀረበ ቢሆንም ችሎቱ ግን ለቅጣት አላማ የወሰደው እያንዳንዳቸው የ700 ሺህ ብር ጥቅም አግኝተዋል የሚለውን የገንዘብ መጠንን ብቻ ነው።

በዚህ መልኩ በፍርድ ቤቱ በተሰጠው የቅጣት ውሳኔ ላይ እና 2ኛ ተከሳሽ ከተከሰሰበት ክስ ነጻ የተባለበት ብይን በሚመለከት ዐቃቤ ህግ ይግባኝ ለማቅረብ ግልባጭ መጠየቁን ለማወቅ ተችሏል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version