አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ የነበረው ሀገር አቀፍ የቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሄደ፡፡
መርሐ ግብሩ ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን÷ አውደ-ርዕዩ እስከ አሁን ድረስ 154 ሺህ 799 በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ሰዎች እንደተጎበኘ ተገልጿል፡፡
በስነ ስርዓቱ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ስለሺ ግርማ ÷ የዘርፉን ተዋንያን ለ1 ወር በአንድ ስፍራ በማገናኘት የተካሄደው አውደ ርዕይ የሚፈለገውን ዓላማ ያሳካ ነበር ብለዋል፡፡
አውደ ርዕዩ በሀገር ውስጥ ላይ ብቻ በማተኮር የተደረገ ቢሆንም በቀጣይ ትላልቅ ዓለም አቀፍ አውደ ርዕዮችን የሚዘጋጅበትን እድል ለመፍጠር ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
ለአውደ ርዕዩ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ እንዲሁም ተሳትፎ ላደረጉ አካላትም ምስጋና ማቅረባቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

