Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሰመራ ከተማ በ1 ቢሊየን ብር ወጪ ለሚገነባው ሆስፒታል የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰመራ ከተማ በ1 ቢሊየን ብር ወጪ ለሚገነባው ደረጃውን የጠበቀ ሪፈራል ሆስፒታል በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

አቶ አወል የመሰረት ድንጋዩን ዛሬ ሲያስቀምጡ እንዳሉት÷ የሚገነባው ሆስፒታል የሰመራ ሎጊያ ከተማን የሚመጥንና ለከተማዋ መገለጫ የሚሆን ነው።

ሆስፒታሉ ለሕብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዲሰጥና ለከተማዋ የሚመጥን ተደርጎ እንደሚገነባ ተናግረዋል።

በዋናው የሀገሪቱ አውራ መንገድ ላይ የምትገኘው ሰመራ ከተማ ላለፉት ዓመታት የሪፈራል ሆስፒታል ሳይኖራት መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡

የሚገነባው ሆስፒታልም ከከተማዋ ነዋሪዎች ባለፈ የከተማዋን ዋናው ጎዳና ለሚጠቀሙ አካላት እንደሚያገለግል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ በበኩላቸው÷ የሠመራና የአካባቢው ነዋሪዎች ለዓመታት ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ደሴ፣ መቀሌ፣ አዳማ እንዲሁም አዲስ አበባ እንደሚጓዙ አስታውሰዋል።

የሆስፒታሉ ግንባታ በሦስት ምዕራፍ ተከፋፍሎ እንደሚገነባ የጠቆሙት አቶ ያሲን÷ የመጀመሪያው ምዕራፍ እስከ 2 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልጸዋል።

Exit mobile version