አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ26 ነጥብ 65 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ሃላፊ መስከረም ደበበ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ ግብር ከፋዮች፣ ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎትና ከውስጥ ገቢ 144 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡
እቅዱን ለማሳካትም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመተግር እና ቀልጣፋ አሰራሮችን በመዘርጋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራትም ከ26 ነጥብ 65 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ነው ሃላፊዋ የተናገሩት፡፡
ከዚህ ውስጥም ከቀጥተኛ ገቢ 19 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር፣ ከማዘጋጃ ቤት 4 ነጥብ 86 ቢሊየን ብር እና ከውስጥ ገቢ 1 ነጥብ 994 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አንስተዋል፡፡
ይህም ከአጠቃላይ ዓመታዊ እቅዱ 18 ነጥ 49 በመቶ መሆኑን ገልጸው÷ ገቢው ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ8 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ የተወሰኑ ደረጃ “ሐ” ላይ የነበሩ ግብር ከፋዮች ወደ “ለ” እንዲሁም ደረጃ “ለ” ላይ የነበሩ ወደ “ሀ” የማደግ እድል እንደነበራቸው አስረድተዋል፡፡
ይህም የገቢ አሰባሰብ ሒደቱ እንዲጨምር ማድረጉን ጠቁመው÷ ግብር ከፋዮች በቀጣይ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ