Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

እንግሊዝ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን በኢትዮጵያ ከእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ አሻደሊ÷ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው ግጭት በርካታ ተቋማት ለውድመት መዳረጋቸውንና በርካታ ዜጎች ላይም ሞትና መፈናቀል መድረሱን አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ ክልሉን ወደ ሰላም መመለስ መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ለአምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የወደሙ ተቋማትን መልሶ የመገንባትና የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት የማቋቋም ስራ ትልቅ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ የአጋር አካላት እገዛ እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ዝቅተኛ መሆኑን፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የጤናና የትምህርት ተቋማት በበቂ ደረጃ እንዳልተሟሉም አብራርተዋዋል፡፡

ክልሉ በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ በርካታ ስደተኞች ማስተናገዱ በተለይ ከሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከጦርነት ሸሽተው ወደ ክልሉ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ክልሉ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ነው አቶ አሻዲሊ የገለጹት፡፡

አምባሳደር ዳረን ዌልች በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራና ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላት በመግለጽ አሁንም ግንኙነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወቅቱን የሱዳን ሁኔታ ተከትሎ የስደተኛ ቁጥር መጨመር እንደሚያጋጥም እንረዳለን ያሉት አምባሳደሩ÷ ተቀብላችሁ በማስተናገድ ረገድ እየተወጣችሁት ላለው ስራ ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡

ሀገራቸው በዩኒሴፍና መሰል ተቋማት በኩል በተለያዩ ዘርፎች ለኢትዮጵያ የሚደረጉ ድጋፎችን እያገዘች መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተገኝተው ስለክልሉ ነባራዊ ችግሮች በተደረገላቸው ገለጻ በቂ መረጃ ማግኘታቸውን ገልጸው÷ እንግሊዝ በቀጣይ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል፡፡

Exit mobile version