አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ምክንያቶች ያለአግባብ የሚባክነውን የህዝብ ሀብት በጠንካራ ኦዲት መከታተል እንደሚገባ የፌደራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ተናገሩ፡፡
22ኛው የዋና ኦዲተሮች እና ባለድርሻ አካላት የምክክር ጉባዔ በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ የፌደራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ÷በኦዲት ግኝቶች ላይ ወቅታዊና በቂ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ኦዲት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት የነበሩ ድክመቶችን በማረም በተወሰደ የኦዲት እርምጃ ሊባክን የነበረ የህዝብና የመንግስት ሀብት ማዳን መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
የህዝብ ሀብት ለታቀደለት የስራ አላማ እየዋለ መሆን አለመሆኑን በኦዲት የመለየትና የችግሩ ባለቤቶችን ለተጠያቂነት የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናልም ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው÷ የክልሉ መንግስት የኦዲት መስሪያቤትን በማደራጀት የመልካም አስተዳደርና የተቋማት አፈፃፀም ውጤታማነትን ለማጎልበት እንዲሁም ግልፀኝነትንና ተጠያቂነትን በማጠናከር የህዝብ ተጠቃሚነት በሚረጋገጥበት መንገድ እየሰራ ነው ብለዋል።
በቢቂላ ቱፋ