Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቀድሞ ደራሼ ልዩ ወረዳ ግጭት በማስነሳት የ75 ሰዎች ህይወት እንዲያልፍ አድርገዋል የተባሉ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀድሞ ደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ የዕርስ በርስ ግጭት በማስነሳት የ75 ሰዎች ህይወት እንዲያልፍና ንብረት እንዲወድም አድርገዋል የተባሉ 42 ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ።

በቀድሞ በደቡብ ክልል በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን የሰዎች ህይወት እንዲያልፍ በማድረግና ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት በማቃጠል ወንጀል የተከሰሱ 42 ተከሳሾች በቀረበባቸው የዓቃቤ ሕግ ማስረጃን እንዲከላከሉ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አርባምንጭና አካባቢው ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ብይን ሰጥቷል።

ችሎቱ ሌሎች 10 ተከሳሾችን በሚመለከት በነጻ እንዲሰናበቱ ብይን ሰጥቷል።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በህዳር 09 ቀን 2015 ዓ.ም እነ ጎብኤል ጎቶ መዝገብ አጠቃላይ 74 ሰዎች ላይ ክስ አቅርቦ ነበር።

በክሱ ላይ ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1(ሀ)፣ አንቀጽ 35፣ አንቀጽ 38 ንዑስ ቁጥር 1/፣ አንቀጽ 238 ንዑስ ቁጥር 1 እና ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚል ክስ ዝርዝር ነበር የቀረበባቸው።

በክሱ እንደተመላከተው፤ ተከሳሾቹ ለጊዜው እጃቸው ካልተያዙ ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በመሆን በህብረት በማደም በቀድሞ በደቡብ ክልል መንግስት በምክር ቤት በ2011 ዓ.ም በአዲስ የኮንሶ ዞን፣ የአማሮ ልዩ ወረዳ፣ የቡርጂ ልዩ ወረዳ፣ የደራሼ ልዩ ወረዳ እና የአሌ ልዩ ወረዳ በሚል መዋቅር መተካቱን ተከትሎ የደራሼ ልዩ ወረዳ ይህን በአዲስ የተዋቀረውን መዋቅር ማህበረሰቡ እንዳይቀበልና እራሳችንን ችለን የጋርዱላ ዞን በመባል በዞን ደረጃ መዋቀር አለብን በማለት የወረዳውን ማህበረሰብ ለግጭት በማነሳሳትና በመቀስቀስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በተለይም ከየካቲት ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በወረዳው ስር በሚገኙ ቀበሌዎች በሆኖታ፣ በሆልቴ፣ በዋሌሶ፣ በጋቶ፣ በሸለሌ፣ በአተያ እና ቀያማ ቀበሌዎች ላይ ማንኛውም የወረዳ አመራር ወደ ስፍራው እንዳይገባ ከገቡም እርምጃ እንዲወሰድባቸው ትዕዛዝ በመስጠትና የጋርዱላ ዞን መዋቅርን ተዋግተን በኃይል እናስፈፅማለን በማለት ለዚህም ተግባር ይረዳቸው ዘንድ ከቀበሌዎቹ ነዋሪዎች ለጥይትና የጦር መሳሪያ መግዣ የሚሆን እያንዳንዱ ነዋሪ ከ100 ብር እስከ 200 ብር መዋጮ እንዲያዋጡ በማስገደድ ገንዘብ መሰብሰባቸው በክሱ ሰፍሯል።

በዚህ መልኩ በተሰበሰበ ብር የተለያዩ የጦር መሳሪያና ጥይት በመግዛት ከየቀበሌው ወጣቶችን በማሰባሰብ፣ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ አጎራባች ዞን ከሆነው ኮንሶ ዞን ስር ካሉ ቀበሌዎች ጋር ረብሻና ሁከት መፍጠራቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።

በዚህ መልኩ የአከባቢውን ፀጥታ ሲያውኩ ከቆዩ በኋላ በሚያዝያ 17 ቀን 2014 ዓ.ም ከኮንሶ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ የሚወስደውን ዋና መንገድ በደራሼ ልዩ ወረዳ ጋቶ ቀበሌ ጤና ኬላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመዝጋት የውጪ ዜጎችን እንዳይንቀሳቀሱ በማስቆም፣ ጥቃት በመፈጸም እንዲሁም በአካባቢው የነበረውን የፀጥታ ችግር ለማስጠበቅ ስምሪት ላይ ባሉ የፌደራል ፖሊስ አባላት እና የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊሶች ላይ ተኩስ መክፈታቸው በክሱ ተዘርዝሯል።

በዚህ ጊዜ አንድ የፌደራል ፖሊስ አባልን በተኮሱት ጥይት በመምታት የአካል ጉዳት እንዲደርስበት ካደረጉ በኋላ ተጎጂዉም በኮንሶ ሆስፒታል ህክምና ሲሰጠው አድሮ ለተሻለ ህክምና ወደ አርባ ምንጭ ይሂድ መባሉን ተከትሎ በነጋታው ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ከአርባ ምንጭ ከተማ፣ ከደራሼ ልዩ ወረዳ ጊዶሌ ከተማ እና ከኮንሶ ዞን ካራት ከተማ የተውጣጡ የፌደራል እና የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ተጎጂውን አጅበዉ በመሄድ ላይ እያሉ በደራሼ ልዩ ወረዳ ሆልቴ ቀበሌ በሚደርሱበት ወቅት ዋና መንገድ በድንጋይ በመዝጋት የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ ተኩስ በመክፈት ባጠቃላይ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የ75 ሰዎች ህይወት እንዲያልፍ ማድረጋቸው በክሱ ዝርዝር ተጠቅሷል።

በተጨማሪም የፀጥታ አካላትን የተለያዩ ንብረታቸውን ዘርፈው በመውሰድ የፀጥታ አካላት ወደ ስፍራው የተንቀሳቀሱበትን 7 ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ባጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 21 ሚሊዮን 525 ሺህ ብር የሆነ ተሸከርካሪዎችን በማቃጠል ከጥቅም ዉጪ እንዲሆን ያደረጉ መሆኑም በክሱ ተመላክቷል።

ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ ዝርዝር እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ በግላቸው እና በመንግስት በተመደበላቸው ተከላካይ ጠበቃ መሰረት ክሱ እንዲሻሻልላቸው የክስ መቃወሚያ አቅርበው ነበር።

ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ እና ዐቃቤ ሕግ ክሱ ሊሻሻል አይገባውም ብሎ ያቀረበው መልስ ተዘዋዋሪ ችሎቱ መርምሮ በመጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት የተከሳሾቹ መቃወሚያ ሊሻሻል አይገባም በማለት ውድቅ ተደርጓል።

ተከሳሾቹ የወንጀል ደርጊቱን አልፈፀምኩም በማለት ክደው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግም ከ13 በላይ የሰው ምስክሮች በችሎት አቅርቦ አሰምቷል፡፡

በአጠቃላይ በ 42 ተከሳሾች ላይ የተሰማው የምስክርነት ቃል እና ተያያዥ የሰነድ ማስረጃ ላይ በወንጀል ድርጊቱ ተሳትፎ እንደነበራቸው ማረጋገጡን በመግለጽ ተከሳሾቹ ተከላከሉ ሊባል የሚገባው ሆኖ ማግኘቱን ገልጿል።

በዚህ መሰረት 8ኛ ተከሳሽ ተገኝ፣ ክሮስ ኪታንቦ፣ ቀኑ ዘነበ፣ ኩሴ ባያቴ እና ዱዱሼ ጨጋቶ የተባሉት አጠቃላይ 42 ተከሳሾች የቀረበባቸውን የወንጀል ድርጊት ስለመፈፀማቸው በቀረበባቸው ማስረጃ መረጋገጡ ተጠቅሶ በተከሰሱበት የወንጀል ህግ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁጥር 142 መሠረት በሙሉ ድምጽ ብይን ተሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ተከላከሉ ከተባሉት ጋር አብረው የተከሰሱትና ፈጸሙት የተባለውን የወንጀል ድርጊት ስለመፈጸማቸው የሚያስረዳ ማስረጃ አልቀረበባቸውም የተባሉ ማለትም 7ኛ፣ 18ኛ፣ 24ኛ፣ 25ኛ፣ 26ኛ፣ ተከሳሾችን ጨምሮ አጠቃላይ 10 ተከሳሾች ከቀረበባቸው ክስ ነጻ በማለት በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ ከሆነ ከእስር እንዲፈቱ ታዟል፡፡

እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው 42 ተከሳሾችን በሚመለከት ግን ፍርድ ቤቱ የመከላከያ ምስክሮች ለመስማት ከህዳር 3 እስከ ህዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ክስ ቀርቦባቸው ከነበሩት 74 ተከሳሾች ውስጥ ይከላከሉና ነጻ ተብለው ብይን የተሰጠባቸው አጠቃላይ 52 ተከሳሾች ናቸው።

በክስ መዝገቡ ተካተው የነበሩ ሌሎች 6 ተከሳሾች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ክሱ የተቋረጠላቸው ሲሆኑ ቀሪዎቹ 16 ተከሳሾች ደግሞ በሌሉበት የታዩ ናቸው።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version