Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሐረሪ ክልል የመሬት ወረራን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በአሁኑ ወቅት ከ20 ሺህ በላይ የሚገመቱ ሕገ-ወጥ ግንባታዎች መካሄዳቸውን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው በክልሉ እየተባባሰ በመጣው ህገ ወጥ መሬት ወረራና ግንባታን መግታት ላይ ያተኮረ ውይይት ከወረዳ አመራር አባላት ጋር አካሂዷል።

የቢሮው ሃላፊ ወ/ሮ አሚና አብዱልከሪም እንደተናገሩት÷በክልሉ እየተስፋፋ ለመጣው የመሬት ወረራና ህገ-ወጥ ግንባታን በተቀናጀ አግባብ መፍትሄ ለመስጠት አመራሩ ወሳኝ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል።

የመሬት ወረራና ሕገ-ወጥ ግንባታ በተለይ በክልሉ በተለምዶ “ሃኪም ጋራ” ተብሎ በሚጠራው የአረንጓዴ ሥፍራዎች ላይ በስፋት መከናወኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት ከ20 ሺህ በላይ የሚገመቱ ሕገ-ወጥ ግንባታዎች መካሄዳቸውን በማሳያነት አቅርበዋል።

የሕገ-ወጥ ግንባታ መስፋፋት በተለይ የሐረር ከተማን ገጽታ ከማበላሸቱ ባለፈ በክልሉ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ችግር እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ሕገ-ወጥ ግንባታን ለመከላከል እርምጃ በመወሰድ ላይ እንደሚገኝ ያመለከቱት ሃላፊዋ÷ ለዚህም የአመራር አባላት ሚና፣ ተሳትፎና ድጋፍ አስፈላጊ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአመራር አባላቱ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከርና በክልሉ ችግረን ለማስቆም ከተዋቀረው ግብረ ሃይል ጋር በመቀናጀት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል።

በክልሉ የሚስተዋለውን የመሬት ወረራና ህገ-ወጥ ግንባታን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ ሃይል እርምጃ ቢወሰድም÷በአንዳንድ ወረዳዎች የሚታየው ቁርጠኝነት ማነስ ድርጊቱን ማስቆም እንዳላስቻለ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዲ ሳኒ ናቸው።

እየተባባሰ የሚገኘውን ህገ ወጥ መሬት ወረራና ግንባታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version