አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጤና ተቋማት ያሉ የእናቶች ማቆያ ቤቶች የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በወሊድ ምክንያት የሚከሰት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ነባር ማቆያ ቤቶችን ለማጠናከር እና በህብረተሰቡ ተሳትፎ አዳዲስ ቤቶችን ለመገንባት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ነዉ ብለዋል።
የእናቶች ሞትን ለመቀነስ የእናቶች ማቆያ ቤት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልፀው፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር መሠረት ዘላለም በበኩላቸው፤ የእናቶች ሞትን ለመቀነስ በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
በግንዛቤ ማጣት፣ ምቹ ትራንስፖርት ባለመኖር እና የጤና ተቋማት ዝግጁነት አናሳ መሆን አሁንም 50 በመቶ የሚሆኑ እናቶች በቤታቸው እንዲወልዱ እያስገደዱ እንደሆነ አመላክተዋል።
ከላይ የተጠቀሱ ችግሮችን በመቅረፍ እንዲሁም ምቹ የእናቶች ማቆያ ቤቶችን በማዘጋጀት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።15:59