Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በ2015 በጀት ዓመት 23 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አግኝተናል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

 

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 በጀት ዓመት በአጠቃላይ 23 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አግኝተናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ ብድርን በተመለከተ ትርጉም ያለው ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ባንኮች ለብድር ካቀረቡት 547 ቢሊዮን ብር ውስጥ 86 በመቶው ለግሉ ዘርፍ የቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

ለግሉ ዘርፍ ከቀረበው ብድር ውስጥ አርሶ አደሩ 15 በመቶ ድርሻ አለው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ከፍተኛውን ብድር የሚወስደው መንግስት እንደነበረ አስታውሰው፤ ይህንን ትርጉም ባለው መልኩ መቀየር ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባንኮች ተደምረው ለግማሽ ሚሊየን ሕዝብ እንዳላበደሩ ጠቅሰው፤ ዋናዋና ተበዳሪ የሚባሉትም በጣም ጥቂት ሺህ ሰዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ቁጠባ እያደገ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ባለፈው ዓመት 17 ነጥብ 8 በመቶ እንደነበር እና ዘንድሮ ወደ 2 ነጥብ 6 ትሪሊየን ለመድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥን ጨምሮ ያለባት እዳ አሁን ላይ 31 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ከዚህም ወስጥ የውጭ እዳችንን ወደ 14 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታትም ከ10 በመቶ በታች ዝቅ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።

በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት በአጠቃላይ 23 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አግኝተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህም ውስጥ ከ7 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነውን ከአገልግሎት ዘርፍ ያገኘነው ነው ብለዋል።

ይህንንም ወደ 25 ቢሊየን ብር ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

Exit mobile version