አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በቻይና ያደረጉትን ጉዞ ተከትሎ 17 የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቻይና በነበራቸው ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል 14 ሥምምነቶች መፈረማቸው ይታወሳል።
ከዚህ ውስጥ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር የሚረዳ ሥምምነት ተፈራርመዋል።
ይህን ተከትሎም በቻይና የኢንዱስትሪና ንግድ ፌዴሬሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ዙ ሌጀንግ የተመራ አምስት የልዑካን ቡድንን የያዘ 17 ኩባንያዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።
ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ በብረታ ብረት፣ በግብርናና በማዳበሪያ ምርትና በሌሎች ኢንቨስትመንቶች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለቸው መገለፁን ኢዜአ ዘግቧል።
ለልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎችና ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎችን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ለኩባንያዎቹ ኃላፊዎች ገለጻ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፥ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
የኢንቨስትመንት መድረኮቹ የሀገራቱን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገውን የኢንቨስትመንት ፍሰት የበለጠ ለማጠናከር አስዋጽኦ ያደርጋሉም ነው ያሉት።