Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በምክክር ሊፈታ የሚችል የሕዝቦች ጥያቄ የፀረ-ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ ሊሆን አይገባም ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በውይይትና በምክክር ሊፈታ የሚችል የሕዝቦች ጥያቄ የፅንፈኛ እና የፀረ-ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ ሊሆን እንደማይገባ የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢና የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ገለጹ፡፡

የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ወቅታዊ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ እና በቀጣይ አቅጣጫ ዙሪያ በደብረ ብርሃን ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ ከወረዳዎች የተውጣጡ እንዲሁም የዞንና የከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ የሠራዊቱ እና የሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮማንድ ፖስቱ ዋና ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብዳታ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ በፅንፈኛው ኃይል ላይ ባሳረፈው ከፍተኛ ምት ብዙዎችን በመደምሰስ የቀሩትን ደግሞ ከእነትጥቃቸው መማረክ ተችሏል፡፡

ይህን ተከትሎም በዞኑ አንፃራዊ ሰላም በመፍጠር የፅንፈኛውን ኃይል ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን የማፍረስ ህልም ማክሸፍ ተችሏል ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሠራዊቱ መስዋዕትነት እየከፈለ የሚገኘው ለሕዝቦች ሰላምና አብሮ መኖር እንዲሁም ለሀገር ሉዓላዊነት እንጂ ሌላ አጀንዳ የለውም ብለዋል የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ፡፡

አሁንም ቢሆን የተበተነውን የፅንፈኛ ኃይል የመመንጠሩ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ጎን ለጎንም የዞኑን የፀጥታ ኃይል የማጠናከር ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡

በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አሕመዲን ሙሐመድ÷ ፅንፈኛው ኃይል በሀገር መከላከያ ሠራዊት በደረሰበት ምት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የደረሰው ችግር በዋነኝነት የአመራሩ ችግር ስለነበረ በክልሉ የአመራር ሪፎርም ተሠርቶ ለውጦች እየተመዘገቡ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

አሁን ላይ አመራሩ ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ይህንን የፅንፈኛ ኃይል በፅናት እየታገለ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version