Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሜ/ጀነራል ክንፈ ከራዳር ግዢ ጋር ተያይዞ በቀረበባቸው ክስ በ3 አመት ከ7 ወራት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነ

 

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 6 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከ111 የራዳሮች ግዢ ጋር ተያይዞ በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው።

የቅጣት ውሳኔውን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም ላይ ጥራቱን ያልጠበቀ 111 ራዳር ከ214 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመግዛት በመንግስት ላይ ጉዳት ደርሷል ብሎ በአራት ተከሳሾች ላይ ነበር የመንግስት ስራን በማያመች አኳኃን መምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የመሰረተው።

በወቅቱ ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት ተከሳሾቹ 1ኛ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው፣ ሌተናል ኮሎኔል ፀጋዬ አንሙት፣ 3ኛ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታ እና 4ኛ የስነምግባርና የህግ ክፍል ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል መሐመድ ብርሀን አብርሃ ናቸው።

ክሱ ከቀረበ በኃላ ግን የሜጀር ጀነራል ክንፈ እና የኮሎሬል መሐመድ ብርሀን መዝገብ ብቻ የቀጠለ ሲሆን ÷ የሌሎቹ ክስ ግን በተለያዩ ምክንያቶች እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ይህም በወቅቱ ቀርቦ የነበረው ክስ ላይ ተከሳሾቹ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር፣ በኮርፖሬሽኑ የሀይቴክ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ የቦርድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የኮርፖሬሽኑ የሥነ-ምግባርና የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ በነበረበት ወቅት የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከግዢ መመሪያ ውጭ ጥራቱን ያልጠበቀ 111 ራዳሮችን ከ214 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በመግዛት በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ በከባድ የሙስና ወንጀል ነው በሚል ነበር በክሱ የቀረበው።

ተከሳሾቹ በ2004 ዓ.ም በኮርፖሬሽኑ የግዢ መመሪያ አንቀጽ 5.1 መሰረት የግዢ ፈጻሚው አካል ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ጥራት ባለው በተቀላጠፈና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በተወዳዳሪ ዋጋ በጨረታ መፈፀም ሲገባቸው መመሪያውን ወደ ጎን በመተው ያለጨረታ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የግዢ ፍላጎት ሳይጠይቅ ሴሌክ (CELEC) እና አሊት (ALIT) ከተባሉ የቻይና ኩባንያዎች ተመሳሳይነት ያላቸውን 111 ራዳሮች መግዛታቸውንና ራዳሮቹ አገልግሎት ሳይሰጡ መቀመጣቸው ተጠቅሶ በክስ መዝገቡ ላይ ተዘርዝሯል።

ከኮርፖሬሽኑ የግዢ መመሪያ ውጪ ያለጨረታና ያለግዢ ፍላጎት 2ኛ ተከሳሽ ሴሌክ ከተባለው ኩባንያ ጋር የገባውን ውል እንዲጸድቅ የሜቴክ ዳይሬክተር ለሆኑት ለ1ኛ ተከሳሽ ደብዳቤ የጻፈ በመሆኑ እና 1ኛ ተከሳሽ ውሉን በማጽደቅ በ2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች በኩል የተፈረሙት ውሎች ጨረታ ሳይደረግ እና የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የግዢ ፍላጎት ሳይጠይቅ የተፈጸመ መሆኑን እንዲሁም ውሉን ያለአግባብ እንዲፀድቅ መደረጉ በክሱ ተገልጿል።

በዚህ መልኩ የቀረበውን ክስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ክሱን በችሎቱ ላይ በንባብ አሰምቶ ነበር።

በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን 8 የሰው እና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ካቀረበ በኋላ ችሎቱ የምስክር ቃል እና ማስረጃዎችን መርምሮ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በተከሰሱበት በወንጀል ህግ አንቀጽ 32 /1 ሀ እና አንቀጽ 411 ንዑስ ቁጥር 2 መሰረት እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ነበር።

በዚህም መሰረት ሜጀር ጀነራል ክንፈ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የቀድሞ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሳሞራ የኑስን ጨምሮ ከ5 በላይ የሰው የመከላከያ ምስክሮችን እና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርበው ነበር።

በተከሳሹ የቀረቡ የመከላከያ ማስረጃዎችን የመረመረው ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች በተገቢው ማስተባበል አለመቻላቸውን አብራርቷል።

በወንጀለኛ መቅጪያ ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 149/1 መሰረት የጥፋቸኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸው ነበር።

ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ህግ የቀረበውን ወንጀሉ የተፈጸመው በጋራ በመሆኑ ቅጣቱ ከብዶ እንዲታይለት ያቀረበውን አስተያየት ሳይቀበል ቀርቷል።

ፍርድ ቤቱ አብረዋቸው ተከሰው የነበሩ ክስ የተቋረጠላቸው ግለሰቦች መኖራቸውን በመጥቀስ እንዲሁም ጉዳያቸው ተነጥሎ ሲታይ የነበሩ ተከሳሾች መኖራቸውን በማብራራት በህብረት የተፈጸመ ለማለት አያስችልም በማለት የዐቃቤ ህግ ማክበጃን አለመቀበሉን ገልጿል።

የሜ/ጀ ክንፈ ዳኘውን አምስት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ግን ፍርድ ቤቱ ይዟል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ የሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው ጥፋተኛ በተባሉበት ድንጋጌ በዕርከን 16 መሰረት በ3 አመት ከ7 ወራት ጽኑ እስራትና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

ይሁንና ፍርድ ቤቱ ሜ/ጀ ክንፈ በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ ከሆነ ከስር መፈታት ይችላሉ ያለ ቢሆንም ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ያላጠናቀቋቸው ክሶች ማለትም ከዕርሻ መሳሪያ ግዢ፣ የመርከብ ግዢ፣ ከሆቴልና ከትምህርት ጋር ተያይዞ በአጠቃላይ በአራት መዝገቦች ገና በፍርድ ቤቱ በመታየት ላይ ናቸው።

በዚሁ ተመሳሳይ የራዳር ግዢ የሙስና ወንጀል ክስ ጋር ተያይዞ ተከሰው የነበሩትና በዚሁ ፍርድ ቤት በ5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው ሲታይ የነበሩት የሜቴክ የህግ ክፍል ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል መሐመድ ብርሀን አብርሃ የቀረበባቸውን ክስ በተገቢው ተከላክለዋል ተብለው በነጻ መሰናበታቸው ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version