አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈውን ‘የመደመር ትውልድ’ መጽሐፍ የማስተዋወቅ ሥነ- ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ÷ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር እና የፓኪስታን ትምሕርት ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ ዋሲም አጅማል ቻውድሪን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
አምባሳደር ጀማል በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የመደመር ፍልስፍና በተለያዩ ዘርፎች ለቀጣናዊ ውኅደት እና ፓን አፍሪካኒዝም ከፍኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡
መደጋገፍን፣ አብሮነትን እና አንድነትን የሚያጎላ የአኗኗር ዘይቤ የሚለው የመደመር ራዕይ በውጤታማነት እየተተገበረ ነው ማለታቸውን የኤምባሲው መረጃ አመላክቷል፡፡
‘የመደመር ትውልድ’ን ጨምሮ በሌሎችም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) መጽሐፍት የተገለጡ ሐሳቦች ለቀጣዩ ትውልድ ትሩፋትን የሚያበረክቱ፣ በትውልዱ መካከል ያለውን ልዩነት በማስተካከል፣ ያለፈውን ጥንካሬና ያለውን ዕምቅ ዐቅም በመጠቀም እንዲሁም ጉድለቶችን በመቅረፍ ረገድ ሁነኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አንስተዋል፡፡
ዋሲም አጅማል ቻውድሪ በበኩላቸው÷ በመደመር ፍልስፍና ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስደናቂ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ተግዳሮቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመቅረፍ ብሎም ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ‘የመደመር ትውልድ’ ሐሳብ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ገልጸው÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለትውልዱ ትሩፋትን ለመተው እየጣሩ መሆናቸውን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ-ፓኪስታን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዛፋር ባክታዋሪ÷ የመደመር ፍልስፍና ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት መመልከታቸውን በሥነ- ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!