Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት ያለመ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት ያለመ የሀገር ሽማግሌዎች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የሀገር ሽማግሌዎች በኢትዮጵያ ያሉ አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት ሚናቸው ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡

በውይይቱ ወቅት የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ታየ ደንደኣ÷ የሀገር ሽማግሌዎች ትክክል የሆነውን በማድነቅ ስህተት የሆነውን በመንቀፍ የተሻለ ነገር መፍጠር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህም የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጠንካራ ተቋም መሆን እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡

የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ÷ ሀገር ሰላም እንድትሆን እና ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስኬታማ እንዲሆን የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች ትስስር ሰብሳቢ ሉባ በየነ ሰንበቶ በበኩላቸው÷ የሀገር ሽማግሌዎች ሲናገሩ የመስማት ባህሉ መቀነሱን በመጥቀስ የሀገር ሽማግሌዎች ልጆቻቸውን ማስተማርና መምከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ሄንክ ጃን ቤከር÷ በሀገራቸው ችግሮች በዲሞክራሲያዊ መንገድ በውይይትና ምክክር እንደሚፈታ በማንሳት ይህ ልምድ በቀላሉ የመጣ እንዳልሆነ አንስተዋል።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ የሀገር ሽማግሌዎች በአንድ መሰባሰባቸው ተስፋን የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኤፍሬም ምትኩ

Exit mobile version