Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ያመዝናል – ኢንስቲትዩቱ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ የሚያመዝን መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ የሰሜን፣ የሰሜን ምሥራቅ፣ የምሥራቅ፣ የመካከለኛው እና የደቡብ ደጋማ ቦታዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ አልፎ አልፎ ባሉ ቀናት ውርጭ የማስከተል ጥንካሬ ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

በሚቀጥሉት 10 ቀናት ለዝናብ መከሰት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ቀጣይነት ይኖራቸዋል፡፡

በዚህም በሰሜን፤ በምሥራቅና በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡

በተጨማሪም በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ዝናቡ ቀጣይነት እንደሚኖረው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ እና በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ የተሻለ የዝናብ ገጽታ እንደሚኖራቸው ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሌላ በኩል አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በመነሳት በተለይም በምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡

Exit mobile version