Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል የኪነ-ጥበብ ምሽቶችን ዳግም ማዘጋጀት ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል የኪነ-ጥበብ ምሽቶችን ዳግም ማዘጋጀት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

ባህል ማዕከሉ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርከስ ማኅበር ጥምረት ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራርሟል።

በመርሸ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፥ የባህል ማዕከሉ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ዘመን ተሻጋሪና የማይረሱ ስራዎችን በማከናወን አስተዋጽኦው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ባልተስፋፉበት ጊዜ ድንቅ የኪነ ጥበብ ስራዎችን ያኖረ መሆኑን ያስታወሱት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ፥ በመሆኑም የማዕከሉን የኪነ-ጥበብ ምሽቶች እንደገና ማስጀመሩ ለዘርፉ እድገት ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ኃላፊ ተስፋዬ እሸቱ (ረ/ፕ/ር) በበኩላቸው ÷ የባህል ማዕከሉ በሀገሪቱ በርካታ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን በማፍራት ባለውለታ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዘርፉ እድገት አሁንም የራሱን አሻራ በማኖር አስተዋጽኦ ለማድረግ በየሳምንቱ ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ ፊልም የሚያሳይ ሲሆን በቀረቡት ፊልሞች ላይ በወር አንድ ጊዜ ውይይት ይደረጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል በ1956 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ማዕከሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ የኪነ-ጥበብ ማሰልጠኛ ማዕከል መሆኑ ይታወቃል።

Exit mobile version