አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 12 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሥራቸውን በመደበኛነት እንዲጀምሩ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ደሳለኝ ጣሰው ተናገሩ፡፡
በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም ችግር ሳቢያ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል ዝግጅት ቢያደርጉም የሰላም ዋስትና እስከሚያገኙ ድረስ ተማሪዎችን ለመጥራት እንደሚቸገሩ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አቶ ደሳለኝ ጣሰው ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙባቸው ከተማዎች ሰላም መሆናቸውን ጠቁመው አንዳንድ ዩኒርሲቲዎች ሥራ እየጀመሩ እንደሆነም ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎችን እንዳይጠሩ የሰላም ችግር አንደኛው ምክንያታቸው ነው ያሉት ሃላፊው፥ የመንገዶች መዘጋት የግብዓት አቅርቦት በፈለጉት መንገድ እንዳያቀርቡ ችግር ሆኖባቸው መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ ዝግጅት እንዲያደርጉ የገበያ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴው የተሟላ መሆን እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡
ነጻ እንቅስቃሴ ተገድቦ በመቆየቱ ተማሪዎችን ጠርቶ ለማስተማር ችግር እንደነበርና አሁን ላይ ችግሮችን እየተሻገሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲዎች በራሳቸው መርሐ ግብር መሰረት ተማሪዎችን ጠርተው ትምህርት መስጠት የሚችሉበት እድል እንዳለም ነው የገለጹት፡፡
የነበረው ችግር ተሻሽሎ እየተቀየረ መሆኑን በማንሳትም ዩኒቨርሲቲዎቹ ግብዓት ለማቅረብ ሲቸገሩበት የነበረው ነጻ የትራንስፖርት እቅስቃሴ ችግር እየተፈታ መሆኑን አስረድተዋል።
ችግሮች እየተፈቱ እንደሚቀጥሉ እና ዩኒቨርሲቲዎችም ሥራቸውን በመደበኛነት እንደሚሠሩም ነው የተናገሩት፡፡